የንግዱ ማህበረሰብ የፖለቲካ ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን እንዲያጋልጥ ጥሪ ቀረበ

85

አዲስ አበባ፣ነሃሴ 30/2013 (ኢዜአ) የንግዱ ማህበረሰብ የፖለቲካ ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንዲወጣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ንግድ ማህበራትና ነዋሪዎች በመስቀል አደባባይ በመገኘት ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል።     

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ካዘጋጃው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ጎን ለጎን ነጋዴው ከመንግስት ጎን በመቆም የኑሮ ውድነቱን እንዲያረጋጋ መልዕክት ተላልፎበታል።     

"ትርፌን እተዋለሁ ደሜን እለግሳለሁ፤ ከትርፍ በፊት አገር ይቀድማል" የሚሉ ሀሳቦችም ተነስተዋል።  

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ ላይ በሁሉት በኩል ጦርነት ተከፍቷል፤ አንዱ በግንባር ወጊያ ሌኛው ደግሞ በኢኮኖሚ አሻጥር ብለዋል።

"የኢኮኖሚ አሻጥሩን ውጊያ በድል ለመወጣት የንግዱ ማህበረሰብ ወታደር ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ያለንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎ ውጤታማ ስራ ሊሰራ አይችልም ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መንግሥት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጉን አስታውሰው ፤አሁን ላይ በሸቀጦች ላይ የዋጋ መረጋጋት እየታየ ነው ብለዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በማጋለጥ ከመንግስት ጋር እንዲሰሩ  ጥሪ አቅርበዋል።

'' ይሄ የእናንተ ግንባር ምሽግ አትቆፍሩበትም፣ተራራ አትወጡበትም፣ቁልቁለት አትወርዱበትም፣የከባድ መሳሪያ ድምጽ አትሰሙም፣ኮቾሮ አትቆረጥሙም፣የውሃ ኮዳ አታንጠለጥሉም ከመኖሪያ ቤታችሁ አትወጡም ከልጆቻችሁ አትርቁም ነገር ግን በዚህ የምታደርጉት ተሳትፎ አገር በማትረፍ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውና ምአልባትም ግንባር ከሚገኘው ሰራዊት ያነሰ ተጋድሎ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም።'' ብለዋል፡፡

 አቶ መላኩ ጨምረው እንደገለጹት ደም መስጠት የታማኝነት፣ ቁርጠኝነት፣ የአይበገሬነት ምልክት መሆኑን የጠቆሙት የንግዱ ማህበረሰብ ከህይዎት ቀጥሎ ያለው ደም ለመስጠት ዝግጁ መሆናችሁን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል ።   

"ዛሬ እዚህ የተገኛችሁ ነጋዴዎች አገርና ህዝብን አትርፋችኋል ይሄን ደግሞ ሌሎች በአርአያነት ሊወስዱት ይገባል ነው ''ያሉት ።

የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት አቅርቦት ላይ እየተሰራ ሲሆን ከ1 ነጥብ 1  ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጤፍ ለማከፋፈል ዝግጁ ሆኗል፤ ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ ምርቶችም በህብራት ሥራ ማህበራት በኩል የሚሰራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የፖለቲካ ተልዕኮ የተቀበሉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱ ፈታህ የሱፍ በበኩላቸው ገበያውን ለማረጋጋት  43 ሺህ ከሚሆኑ ነጋዴዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት  መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ግን ወደህጋዊ  መስመር መግባት ያልቻሉ  ከ2 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም