አርሲ ዞን በአግባቡ ከተሰራበት ሃገር የሚቀልብ የግብርና ምርት ማግኘት ይቻላል–ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

343

አዳማ  ነሃሴ 30/2013 (ኢዜአ)  የአርሲ ዞን በአግባቡ ከሰራንበት ከኦሮሚያ አልፎ ሀገር የመቀለብ አቅም አለው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ በአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ሻቂ ሸረራ ቀበሌ በኩታ ገጠም የተዘራውን የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለፁት የአርሲ ዞን በአግባቡ ከሰራንበት ከኦሮሚያ አልፎ ሀገር የመቀለብ አቅም ያለው ዞን ነው ብለዋል።

አርሲ ዞን ከሀገሪቱ አካባቢዎች ትልቁን የሰብል ምርት ድርሻ የሚይዝ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሽመልስ፤ የግብርና ዘርፍ ዘመናዊነት መነሻ መሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኦሮሚያ ግብርናን ጨምሮ ሰፊውን የሀገሪቷን የኢኮኖሚ ሴክተር የሚያንቀሳቅስ ክልል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ያሰብነውን የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን የምናደርገው የዚህ መሰሉን እምቅ ሀብት መነሻ በማድረግ በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ላይ ስንሰራ ነው ብለዋል ።

በአርሲ ዞን ሻቂ ሸረራ ቀበሌ ከ1ሺህ 100 ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን ከ900 በላይ የሚሆነው ደግሞ ስንዴን በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ሁሴን አመልክተዋል።

“በዞኑ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላና ሌሎች ሰብሎችን ጨምሮ ከ13ሺህ በላይ የኩታ ገጠም አሰራርን በማደራጀት የአርሶ አደሩን የተበጣጠሰ ማሳ በአንድ ላይ በማሰባሰብ እያለማን ነው” ብለዋል።

በዞኑ ከ583 ሺህ ሄክተር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ከዞኑ ግብርና የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት ከጉብኝቱ ጎን ለጎን ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን የአርሲ ዞን ከተማ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ህንፃም አስመርቀዋል።

በጉብኝቱ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የስራ ሃላፊዎች የአርሲ ዞንና የአሰላ ከተማ ነዋሪዎችም ተገኝተዋል።