በቤልጂም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ለመከላከያ ሰራዊትና ለተጎዱ ወገኖች ከ8 መቶ ሺህ ብር በላይ አሰባሰቡ

78

ነሀሴ 30/2013 (ኢዜአ) በቤልጂም ብራስልስና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ለተጎዱ ወገኖች ከ8መቶ ሺህ ብር በላይ ማሰባሰባቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በቤልጂየምና የአውሮፓ ህብረት የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ በቤልጂየም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ለመደገፍ እያደረጉት ስላለው ድጋፍና መድረኩን ለመታደም በመገኘታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው በቤልጂየም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና የሃብት ማሰባሰብ ተግባራትን በማከናወን የአገራቸው የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን አስመስክረዋል ብለዋል፡፡

በሃገር ውስጥ ያሉ ዜጎች የክተት ጥሪውን በመቀበል ጦሩን በመቀላቀል ከሚያደርጉት ተሳትፎ በተጨማሪ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚሆን ሃብት ማሰባሰባቸውን ጠቅሰው፣ ዳያስፖራውም የጀመረውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የሃብት ማሰባሰብ ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሃገራቸው በማካሄድ ላይ ያለችውን የህልውና ዘመቻ ለመደገፍና የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ ሁልጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በዚሁ መሰረት በዕለቱ ካሰባሰቡት 14,500 ዩሮ እና 500 የአሜሪካን ዶላር (ከ800 ሺህ ብር በላይ) በተጨማሪ በቋሚነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

ዳያስፖራው ገንዘብ ወደ ሃገር ቤት ሲልክ በህጋዊ መንገድ ብቻ በመላክ ለሃገራዊ የውጭ ምንዛሪ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ማሳሰባቸውን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም