በአገር ውስጥ የሚመረት የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት ይሰራል

283

ነሀሴ 30 /2013 (ኢዜአ) በአገር ውስጥ የሚመረት የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከመድኃኒት አቅራቢዎች እና ሌሎች ባለድርሸ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት እያደረገ ነው፡፡

የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ቀጣይ ማሻሻል የሚቻልባቸውን አቅጣጫዎች ማመላከት መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ አለምፀሐይ ጳውሎስ፤ የመድኃኒት አቅርቦትን ችግርን ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

መንግስት የዜጎችን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለዘርፉ ስኬት የመድሃኒት አቅርቦት መሟላት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ 85 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ የመድኃኒት አቅርቦት ከውጭ የሚገባ በመሆኑ በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነው አነስተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የአገር ውስጥ ምርት የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ በመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የሁሉም ባለደርሻ አካላት ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።