የአሸባሪው ህወሃት ነገረ ስራ ‘እኔ ከምጠፋ የትግራይ ወጣት፣ ሕፃናት፣ ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ይለቁ’ ነው - አርቲስት ደበበ እሸቱ

135

"ሚሲዮናዊያን ወደ አፍሪካ ሲሙጡ" አሉ ዴዝሞንድ ቱቱ "እነሱ መፅሐፍ ቅዱስ እኛ ደሞ ሃገር ነበረን። መፅሐፍ ቅዱስ ሰጡንና እንፀልይ ሲሉን መፅሐፍ ቅዱስን ይዘን አይናችንን ጨፍነን ፀሎታችንን ጨርሰን ዐይናችንን ስንገልጠው፣ እኛ መፅሐፍ ቅዱስ ይዘናል እነሱ ደግሞ ሃገራችንን ላይለቁ ያዙ"።

ከዚሁ ጋር በተመሳሰለ መልኩ ሶሻል ኔትወርኪንግ ሲያመጡ እነሱ ዋትስአፕና ፌስቡክ ነበራቸው እኛም ነፃነት ነበረን። ነፃ ነው ሲሉን ዐይናችን በነፃው የፌስቡክ ሲጨፈንና ስንገልጠው እኛ ፌስቡክና ዋትስአፕን አግኝተን የነሱ ሱሰኛ ሆነን እነሱ ደግሞ የነጻነታችን ወሳኞች ሆኑ።

ማንኛውም ነገር "ነፃ" ነው ሲባል የሚያስከፍለን ዋጋ እስከ ነፃነታችንን ማጣት ነው። አሁንም የተለመደውን ለማድረግ ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት። ከሃዲዎቹ፣ አሸባሪዎቹ፣ እኩይ ተግባራት ሲፈጠሩ ለሱ መሞከሪያነት የተሰሩ የእንግዴ ልጆች የሚፈፅሙትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የማየት አቅም የተነፈጉት ከጁንታው በላይ ጂኒዎቹ ድጋፋቸውን ለድርጊታቸው ማስፈፀሚያ በመቸር፣ ሰላማዊዉን የሃገሪቱን ሠራዊት አባላት፣ አብሯቸው ሲያርስ፣ ሲዘራ፣ ሲያርም ሲወቃና ወደ ጎተራ ሲያስገባላቸው፣ ከጥቃትም ሲከላከልላቸው፣ እንደ ወንድም ያመናቸውን ሰራዊት፣ በተኙበት ሲጨፈጭፋቸው አንድም ቃል አልተነፈሱም።

ይህም የወንጀሉ ደጋፊ ሳይሆኑ የወንጀሉ አካል መሆናቸውን ማረጋገጫ ነው። አሁንም እንደገና ገንዘብ እንቸራችሁዋለን በነፃ ብለው አይናችንን አስጨፍነው ሕዝብ የተፋውን ከሃዲ፣ ሀገር ዘራፊ፣ መልሰው ሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ ነው ጥረታቸው።

ብሔራዊ ሠራዊቱ "የትግራይ ሕዝብ ከሚጠፋ እኔ ልጥፋ" በሚል መርህ የሚንቀሳቀስ ሕዝባዊ ሠራዊት ሲሆን ጁንታው ፋሺስት ግን "እኔ ከምጠፋ የትግራይ ወጣትና ሕፃናት፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች ይለቁ" ብሎ ነው ጦር በመስበቅ ላይ ያሉት።

ይህን ግልፅ የሆነ ልዩነት፣ በተግባራቸው ያሳዩትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት፣ የሕፃናቱን ከአቅማቸው በላይ የሆነ የጦር መሳርያ ጁንታው አስታጥቆ ማሰለፉን አይተው እንዳላዩ ሆነው በዝምታ ማለፋቸው ምን ያህል ወገንተኛ እንደሆኑ፣ የወገንተኝነታቸውም መንስኤው ከነዚህ የእንግዴ ልጆች ወደ ስልጣን መመለስ ሊያስገኝላቸው የሚችለውን ጥቅም በማይጨበጥ ተስፋ እየቃዡት መሆኑ በቂ ማስረጃ ነው።

በእንዲህ አይነት ወሳኝ ወቅት ማንነታችን በአግባቡ ሊፈተሽና በወቅቱ ጉዳይ ላይ የት እንደቆምን በእርግጠኛነት ማሳወቅ ያስፈልገናል።

ይህ ጥያቄ አይደለም፣ ማግባባትም አይደለም፣ ግዴታን ለመወጣት መብቃት አለመብቃትን ማጥራት እንጂ! ሃገር ጥሪ ስታቀርብ ለልጆቿ ሁሉ ነው።

የምትጠረጥረው የላትም፣ ሁሉም ልጆቿ በመሆናቸው ታምናቸዋለች። ክደዋትም እናትነቷን በመሃላ ሲፍቁትም እናት ነችና ላለመለወጥ ትመክራለች፣ ታስመክራለች። ሁሉም ነገር ዳርቻ አለውና ጥቂቶቹ ከሃዲ ልጆቿ ብዙሃኑን እናታችን ብለው የፀኑትን ጉዳት ብርታቱን ስታየውና ሲብስባት ታግሰው ከቆዩ መልካም ልጅቿ ላይ ትእግስታቸውን በምርቃት አጅባ ትለቃቸዋለች።

ይህ ነው አሁን እየሆነ ያለው፣ የሆነውም፣ በመሆንም ላይ ያለው። ለነዚህ ከሀዲዎች ቃል ተገብቶላቸው፣ከውጭ ሃይሎች ጋር በመወገን፣ ተላላኪም ቅጥር ነፍሰ ገዳይነትም እንዲያካሂዱ እጃቸውን ተስመው፣ ኪሳቸውን በፋይናንስ አስሞልተው፣ ለስልጣናቸው መመለስ ቃል ተገብቶላቸው፣ ጃስ ተብለው ትእዛዝ ተቀብለው በሃገርና በሕዝብ ላይ ተነግሮ የማያልቅ ግፍ አወጁ።

ወጣቱን በማይጨበጥ የቁም ቅዠት ተስፋ ሆዱን ሞልተዉት ለዛ በሌለው ድንፋታ ድል እየተገኘ ነው ቱሪ ናፋ ጆሮውን ሲያደነቁሩት መጨረሻቸው፣ "ዓይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች" ሆነው በእምቢታ የተቸራቸውን የሰላም ጥሪ አሻፈረን እንዳላሉ አሁን ተንበርክኮ "አደራድሩን" በምንም መልኩ በማንም ምልጃ የሚገኝ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በተሰጣቸው አደራ ሃገርንና ሕዝብን የደፈረን፣ የጨፈጨፈን፣ ከሥርአት ውጪ አብጦ በውጪ ሃይሎች ተማምኖ የበደለን ቡድን የሚሰሙበት ጆሮ የላቸውም፣ ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ ያረጋገጡት አቋማቸው ነው።

የሚሰሙት ነገር ቢኖር አደራድሩን ባዮች እጃቸውን ሰጥተው ለሕግ ለመቅረብ እራሳቸውን ለምርኮ ሲያቀርቡ ብቻ ይሆናል፣ ከዚህ ውጪ አማራጭ አይኖርም። ድል የማይተካ ሕይወታቸውን ለሀገርና ሕዝብ ለሰጡን በየግንባሩ ለሚገኙት ጀግኖቻችን፣ ለጀግኖቻችን ደጀን ለሆነው ሕዝብ፣ ብቃት እውቀትና ችሎታ ላሳዩን አመራሮች ምስጋናችንና አክብሮታችንን ድጋፋችንን በመቀጠል እናረጋጥላቸዋለን!።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም