የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ዕንቁ አርቲስት አለማየሁ እሸቴ

168

ነሀሴ 29 /2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ከሚነሳ ድምጻዊያን መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳል አርቲስት አለማየሁ እሸቴ።

የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ከፍወዳለ ደረጃ ካደረሱት ድምጻዊያን መካከል እንደሆነም ይነገርለታል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ በኢትዮጵያ የግል ሸክላ ሙዚቃ ሕትመት ታሪክም በአምሃ ሪከርድስ አማካኝነት የሙዚቃ ሸክላ ያሳተመ ዘመናዊ የሙዚቃ ባለሙያ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በአብዛኛው ባለፉት 50 ዓመታት የነበረው የኢትዮጵያ ሙዚቃ በባህላዊ ሙዚቃዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደነበር ይገልጻሉ።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ባህላዊው ሙዚቃ ወደ ዘመናዊነት ሽግግር በሚያደርግበት ወቅት የተፈጠረ ድምጻዊ ነው ማለት እንደሚቻል ተናግረዋል።

አርቲስቱ የተጫወታቸው ሙዚቃዎች ዘመናዊነትን የተላበሱ መሆናቸውንና የሙዚቃ ሥራዎቹ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ መደመጥ የሚችሉ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

አብዛኞቹን ሙዚቃዎች የደረሳቸው ራሱ አርቲስት አለማየሁ መሆኑን የሚገልጹት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ሥራዎቹም ሕዝባዊ ተወዳጅነት ያገኙ መሆናቸውን አውስተዋል።

አርቲስቱ በሙዚቃ ሥራዎቹ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃ ወቅት የሚያሳያቸው ትዕይንቶችና አለባበሱ የዘመናዊነቱ መገለጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ሙዚቃዎቹ አገርን፣ ትምህርትን፣ ፖለቲካና ሌሎች መስኮችን የዳሰሱ ሁሉን አቀፍ ይዘትና ሥራዎቹ አስተማሪ እንደሆኑም ነው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ የገለጹት።

አርቲስቱ የሙዚቃ ሥራዎቹ ኢትዮጵያዊነትን የዳሰሱ መሆናቸውን ለማወቅ ዜማዎቹን ማዳመጥ ብቻ በቂ ነው፤ ድምጻዊው በእናት አገሩ ጉዳይ ድርድር የማያውቅ ነው ብለዋል።

የአርቲስት አለማየሁ እሸቴ በሙዚቃ ሥራዎቹ ለቀጣዩ ትውልድ ስንቅ የሚሆኑ ሥራዎችን ትቶ ማለፉንና ከሥራዎቹ ብዙ ትምህርቶችን መቅሰም እንደሚቻል አስረድተዋል።

አንጋፋዊ ድምጻዊ ለሙዚቃ ያለው ፍቅርና ለሙያው ያለው ክብር ለአሁኑ ትውልድ የጽናት ተምሳሌትነትን የሚያስተምር እንደሆነ ነው የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ የተናገሩት።

የአርቲስት አለማየሁ እሸቴን ጨምሮ ሌሎች በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አሻራቸውን ያሳረፉ ድምጻዊያን ታሪክ ተሰንዶ ትውልድ እንዲማርባቸው ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ ከትናንት በስቲያ ባደረበት የልብ ሕመም ምክንያት በ80 ዓመቱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወቃል።

አርቲስቱ  የአራት ወንዶች እና የሦስት ሴት ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፤ አራት የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅቷል።

የድምጻዊው ሥርዓተ ቀብር ጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም