ለሃገራችን ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከአካባቢያችን እስከ ዳር ድንበራችን ድረስ እንሰለፋለን

264

ጭሮ፣ነሐሴ 29/2013(ኢዜአ) የሃገራችንን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አካባቢያችንን ከመጠበቅ ጀምሮ እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት እንሰለፋለን ይላሉ በጭሮ ወረዳ መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና የወሰዱ ነዋሪዎች።

መሰረታዊ የማህበረሰብ አቀፍ ወታደራዊ ስልጠናውን ወስደው ካጠናቀቁት ነዋሪዎች መካከል በወረዳው መድቾ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሀመድ አልዪ አንዱ ናቸው።

የአገር ሀብት ዘራፊና የህዝብ ሰላም አደፍራሽ የሆኑትን ሸኔንና ህወሓትን ለማጥፋት ከአካባቢያቸው ጀምሮ እስከ ሀገር ዳር ድንበር መከታ የመሆን አላማን ሰንቀው መሰረታዊ ስልጠናውን መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ልክ እንደ እርሳቸው ሁሉም በአካባቢው ሰላም ጉዳይ በይመለከተኛል መንፈስ እንደሚሰራና ሁሌም ዝግጁ ሆኖ በንቃት ጥበቃ ለማድረግ መነሳቱን ገልጸዋል።

ሌላዋ የስልጠናው ተሳታፊ ወጣት ቀሽትና ደነቀ በበኩሏ “ሴቶችም ከአካባቢያቸው በመጀመር ሀገርን ከአጥፊዎች የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን መወጣትአለባቸው” ብላለች፡፡

በሴቶች ላይ ግፍ ሲፈፅም የነበረውን አሸባሪ ሀይል ለማጥፋት እራሷን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ሁሉ በጀግንነት መንፈስ ስልጠና ወስደው ዝግጁ ሆነው ለራሳቸውና ለሌሎች መከታ መሆን አለባቸው ነው ያለችው፡፡

አቶ ጀማል አደም በጭሮ ወረዳ የኢጀፋራ ቀበሌ ነዋሪ እንዳሉት እያንዳንዱ ነዋሪ የአካባቢውን ሰላም ማስከበር እንዲችል የአቅምና ስነ-ልቦና ግንባታ መሰረታዊ ስልጠናው እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ፡፡ 

“ሁላችን ሰላምና ደህንነታችንን በቤታችንንና በአካባቢያችን የማረጋገጥ ትልቅ ሃላፊነትን በዚህ ስልጠና ተረክበናል” ብለዋል።

የጭሮ ወረዳ ፖሊስ ምክትል ዳይሬክተር ዋና ሳጅን ግርማ ተስፋዬ በጭሮ ወረዳ ከ39ኙም ቀበሌዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች የእድሜ ክልል እና ጾታ ሳይገድባቸው በስልጠናው ተሳታፊ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ማህበረሰቡ ባለው አቅምና መሳሪያ ሁሉ ለአካባቢውና ለሀገሩ ደጀንና መከታ ለመሆን መዘጋጀቱንም ዋና ሳጂን ግርማ ተናግረዋል፡፡ 

አያይዘውም ሰልጣኞች በወሰዱት ስልጠና ታግዘው መንደርና ሀገራቸውን ለመጠበቅ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ አሳስበዋል፡፡

ለ15 ተከታታይ ቀናት የተሰጠውን መሰረታዊ ስልጠና ተከታትለው ያጠናቀቁት ሰልጣኞችም በቀበሌያቸውና በሀገር ደረጃ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በንቃት ለመስራት ቃለ መሃላ ፈፅመዋል፡፡