የማህበረሰብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎ ለማሳደግ ብዙ መስራት ይገባል

109

ነሀሴ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የማህበረሰብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎ የበለጠ እንዲያድግ ብዙ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የ2013 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ፣ የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ እንደገለጹት፤ የማህበረሰብ ስፖርት የህብረተሰቡ ጤና በመጠበቅ፣ አገሪቷ ለመድሐኒት የምታወጣውን የውጪ ምንዛሬ መጠን በመቀነስ፣ የእርስ በእርስ ትስስር በመጨመርና ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና አለው።
በኢትዮጵያ በመንግስት ደረጃ ይህን ለማስፋፋት ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ህብረተሰቡ በተሳትፎ የሰጠው ምላሽ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም "የብዙሃን የማበረሰብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊዎችን ቁጥር ለማሳደግ ብዙ መስራት ይገባል" ብለዋል።
በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የእቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት፤ በነሃሴ ወር ብቻ ለሶስት ቀናት በተካሄደ የጤናና አካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መርሃ ግብር ለአገር መከላከያ ሰራዊት የተሰበሰበው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቀላል አይደለም።

በቀጣይም የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩ ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር አባላት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት መንግስት ለማህበረሰብ ስፖርት የሰጠው ትኩረት ያህል እንዳልተሰራ ነው ያስታወቁት።
ለዚህም እንደ ችግር ያስቀመጡት የኮቪድ 19 እና የስፖርት አመራር አባላት የቁርጠኝት ችግር መሆኑን ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን የውድድር ስፖርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በአንዳንድ የስፖርት ማህበራትና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያለው ውዝግብ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የስፖርት ማዘውተሪ ቦታዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ የይዞታ ካርታ የሌላቸውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማቀናጀት ካርታ እንዲሰራላቸው የማድረግ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዴየሞች ግንባታ ስራም ትኩረት እንደሚሻ ነው የገለጹት።
አሁን ላይ የባህር ዳር ስታዴየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች እንዲያካሂድ የተመረጠ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ያለመጠናቀቁ ተነስቷል።

በመሆኑም የባህር ዳር ስታዴየም ጨምሮ ሌሎች ስታዴየሞች አቅም በፈቀደ ልክ ግንባታው እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የውይይቱ ተሳታፊዎችን እንደ አገር ከውስጥና ከውጭ ያለው ጫና በአጭር ጊዜ በአሸናፊነት ለመወጣት የስፖርት ቤተሰቡ የራሱን አሻራ በማሳረፍ የሚጠብቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም