በኢትዮጵያ የደን ሽፋኑ 17 በመቶ ደርሷል - የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን

145

አዳማ ፣ ነሃሴ 29/2013/ኢዜአ / ባለፉት ዓመታት በአካባቢ ጥበቃ ላይ በተሰሩ ስራዎች የሀገሪቷ የደን ሽፋን 17 በመቶ መድረሱን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ከአስሩ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች የተውጣጡ የዘርፍ ሴክተርና ባለድርሻ አካላት ጋር ያለፈውን ዓመት የስራ አፈፃፀም በአዳማ ከተማ እየገመገመ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ ላይ በተሰሩት ስራዎች የሀገሪቱ የደን ሽፋን 17 በመቶ ደርሷል።

በየጊዜው በተፈጥሮ ሀብት ላይ በሚደርሰው ጉዳት በተለይ የእርሻ መሬት ለማስፋፋት፣ ግጦሽ፣ ሀገ-ወጥ ሰፈራና ምንጣሮ የሀገሪቷ የደን ሽፋን ወደ 3 በመቶ ወርዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

በ2013 ዓ.ም በተካሄደው የደን ሀብት ቆጠራ ሽፋኑ 17 በመቶ ላይ ደርሷል ያሉት ኮሚሽነሩ አሁን የተገኘው ውጤት ባለፉት ሶስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የተተከሉትን ችግኞች አያካትትም ብለዋል።

ወደ አካባቢ የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን ከመቀነስ አኳያ የልማት ፕሮጀክቶች በሚኖራቸው አካባቢያዊ ተፅዕኖ ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራ መሰራቱንም አመልክተዋል።

የውሃና የአየር ንብረት ብክነት ለመቀነስ፣ ለካርበን ሽያጭ ምቹ መደላድሎችን ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።

በኮሚሽኑ የዕቅድና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ነስሩ አወል በበኩላቸው "በበጀት ዓመቱ ሶስተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በማስተባበር ችግኞች በበቂ ሁኔታ እንዲዘጋጁ በማድረግና የአካባቢና የውሃ ብክለትን ከመከላከል አንፃር የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግበናል" ብለዋል።

እንደ አቶ ነስሩ አወል ገለፃ የአዋሽ ወንዝን የውሃ ብክለት መጠን ለመለየት በቆቃ፣ በሰቃና በወንዙ ወራጅ ውሃ ላይ በተካሄደው ጥናት ብክለቱ ከተቀመጠው ደረጃ በላይ መሆኑ ተረጋግጧል” ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከፌዴራል፣ ከኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ አስተዳደርና ተፋሰሶች ልማት ሴክተር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተመሳሳይም የኢንቨስትመንት ተቋማት አካባቢያዊ ተፅእኖ ለመለየት በኦሮሚያና አዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው ጥናት 34 የሚሆኑት ደረጃቸውን አሟልተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቷ 16 ዋና ዋና ከተሞች የድምፅ ብክለት ጥናት መካሄዱን በመግለፅ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ግብረ መልስ መሰጠቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም