አይኮም ኢትዮጵያ 450 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አይኮም ኢትዮጵያ 450 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29፤2013 (ኢዜአ) አይኮም ኢትዮጵያ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በአዲስ አበባ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ግምቱ 450 ሺህ ዶላር የሆነ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
መሰረቱን በአሜሪካ ያደረገው ድርጅቱ በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር 450 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸውን የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የሕክምና ቁሳቁሱን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፈቲያ መሐመድ ተረክበዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ጥበቡ አለማየሁ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ድጋፉ መሰባሰቡን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያዊያን የተሰበሰበው ድጋፍ 'ወገኖቻችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንዳይጎዱ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ያቃልላል' ብለዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፈቲያ መሐመድም 'ሁሉም ከተረዳዳ የማንፈታው ችግር የለም' በማለት ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የሕክምና ቁሳቁሱ በክፍለ ከተማው ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እንደሚከፋፈልና ለኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።