በምዕራብ ጎንደር ዞን 343 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፈነ

248

መተማ፣ ነሐሴ 29/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በ2013/14 ምርት ዘመን 343 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ በምርት ዘመኑ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ወንድይፍራው ሙሉዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዞኑ ካለፉት ዓመታት በተሻለ የተመረጡ የሰብል ዓይነቶት በኩታ ገጠምና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመከተል በማልማት ላይ ይገኛል።

በዚህም ከ395 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 343 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።

በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆነው በኩታ ገጠምና ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መልማቱን ኃላፊው ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩና በባለሃብቶች ከሚለሙት ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎ ይገኙበታል ብለዋል።

ቀሪው   መሬት ከዚህ በኋላ ተዘርተው በሚደርሱ ጤፍ፣ ሽንብራና ፈጥነው የሚደርሱ ማሽላ ዝርያዎች እንደሚሸፈን አቶ ወንድይፍራው አስረድተዋል።

”በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከሎችና በሞዴል አርሶ አደሮች እየተሰሩ ያሉ የሰርቶ ማሳያዎች ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ በማስጨበጥም እያገዙ ይገኛል” ብለዋል።

ከህልውናው ዘመቻ ጎን ለጎን የገበሬዎች ቀን በማዘጋጀት አርሶ አደሮች ልምድ እንዲለዋወጡ ከወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።  

በቋራ ወረዳ ፋርሻሆ ቀበሌ  አርሶ አደር ግዛቸው መለሰ ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ምክረ ሃሳብ መሰረት ካላቸው 10 ሄክታር መሬት ውስጥ ሁለት ሄክታር በአኩሪ አተር ሰብል ማልማታቸውን ገልጸዋል።

ቀሪው መሬት በሰሊጥና ማሽላ ከመሸፈናቸውም በተጨማሪ ጤፍ ለማልማት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የአካባቢው  ነዋሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ በበኩላቸው ፤ ያላቸውን መሬት በሰሊጥ፣ ማሽላና አኩሪ አተር  የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም ማልማታቸውን ገልጸዋል።

 ከሚያለሙት መሬት ከ750 ኩንታል ያላነሰ ምርት እጠብቃለሁ ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር  ዞን ባለፈው የምርት ዘመን 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።