ማህበሩ ለተፈናቃዮች ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች ድጋፍ አደረገ

ደሴ፣ ነሐሴ 29/2013 (ኢዜአ) የጤና፣ ልማትና ፀረ ወባ ማህበር በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ደሴና ኮምቦልቻ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች 1 ሚሊዮን 830 ሺህ ብር የሚገመቱ ቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡

የማህበሩ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ዶክተር አበረ ምህረቴ  እንደገለጹት፡ ድጋፉ   2 ሺህ 700 ብርድ ልብስ፣ 26 ሺህ 400 የሴቶች ንጽህና መጠበቂያዎችን ያካትታል።

ድጋፉ በአሜሪካ ከሚኖሩ የጎጃም ዕድር አባላትና ደጋፊዎች ጋር በመተባበር መሰባሰቡንም ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድጋፉ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

መንግሥት ህብረተሰቡንና ተቋማትን በማስተባበር የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ ድጋፉ በየዕለቱ ከሚጨምረው ተፈናቃዮች ቁጥር ጋር ስለማይጣጣም አቅም ያላቸው ልገሳ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመጠለያ ጣቢያዎቹ  ከ 233 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ኃላፊው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም