ቀጥታ፡

በፈጠራ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶች እውቅና ተሰጣቸው

ነሀሴ 28/2013 በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ወጣቶቹ "ትፍጠር ኢትዮጵያ" በሚል መጠሪያ ስር በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና መንግስታዊ ባልሆኑ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ ናቸው።

የፈጠራ ባለሙያዎቹ "ለኮቪድ-19 አገር በቀል መፍትሄ" በሚል መሪ ሃሳብ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን አበልጽገዋል፡፡

ወጣቶቹ የኤክስሬይ የኮቪድ መመርመሪያ ስካነር፣ ከንክኪ ነፃ የሆኑ የእጅ መታጠቢያዎች፣ ለሆስፒታልና ለሆቴል ክፍሎች የሚገጠሙ አየርን ከብክለት የሚያፀዱ ማሽኖች፣ ሜካኒካል ቬንትሌተርና ሌሎች የፈጠራ ስራዎችን አበረክተዋል።

የመድኃኒቶች አጠቃቀምና ሌሎች መረጃዎችን የያዙ የኦን ላይን ድረ-ገፆች፣ በመኪና ላይ የሚገጠሙ የተሽከርካሪውን የጉዞ ሁኔታ መቆጣጠርና ኮንትሮባንድን ለመከላከል የሚያግዙ ፈጠራዎችም ይገኙበታል።

በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ መንግስት አገር በቀል ፈጠራን ለማበረታታት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ኮቪድ-19 አገር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በተወሰዱ ጠንካራና ቀጣይነት ያላቸው ጥረቶች ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎቹ የሰሯቸው ቴክኖሎጂዎች ችግሮችን በአገር ውስጥ እውቀት መፍታት የሚያስችሉና የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፈጠራ በአግባቡ ከተመራ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ቀጣይነት ያለው እድገት ማረጋገጥ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

ፈጠራን ለማበረታታት መንግስትና የግሉ ዘርፍ ሚና ስለሚጠበቅ እንደ አገር ድንበር የለሽ ቅንጅት መኖር አለበት ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሚኒስትሩ የፈጠራ ክህሎት እንዲዳብርና ወደ ውጤት እንዲቀየር ያላሰለሰ ድጋፍ ላደረጉ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አገራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም