ለበዓል የምርቶች እጥረት እንዳይከሰት ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ

80

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 28/2013(ኢዜአ)  ለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል የምርቶች እጥረት እንዳይከሰት ከአምራቾች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሲሳይ አረጋ፤ በሰጡት መግለጫ ኤጀንሲው መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በቀጥታ ከአምራቾች በማስገባት ገበያ ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ በሚገኙ 148 መሠረታዊ የሸማቾች ሕብረት ስራ ማህበራትና 10 የሸማች ዩኒየኖች ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ማቅረብ መጀመራቸውንም ነው የገለጹት።

የግብርና ምርቶችን በማቅረብ ረገድ በክልሎች ከሚገኙ የአምራች ሕብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ምርቶችን ደግሞ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቀጥታ የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርቶቹን ወደ መዲናዋ እንዲገቡ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል።

በህብረት ስራ ማህበራቱ በኩል ወደ መዲናዋ እየገቡ ከሚገኙ ምርቶች መካከል በሬ፣ በግ፤ ፍየል፣ ዶሮ እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅዖ ውጤቶችን ጨምሮ ቀይ ሽንኩርትና ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎች ይገኙበታል።

የዱቄት አቅርቦትም ለህብረተሰቡ  በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቶ እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በህብረት ስራ ማህበራቱ የፍጆታ ሸቀጦችን በማቅረብ ገበያን በማረጋጋት ረገድ የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ መቆየታቸውንም አንስተዋል።

በአዲስ አበባ የጳጉሜን ቀናቶች “አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የድል ነፀብራቅ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም