የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሸባሪው ህወሃት በጨጨሆ መድሃኔ አለም ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰውን ጉዳት አወገዘ

ደብረ ታቦር፣ ነሐሴ 28/2013 (ኢዜአ) የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሸባሪው ህወሃት በጨጨሆ መድሃኔ አለም ቤተ ክርስቲያን ላይ ባደረሰው ጉዳት ማዘኑን በመግለጽ ድርጊቱን አወገዘ።

የጉባኤው አባላትና ሌሎች አጋር አካላት በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በቦታው ተገኝተው ተመልክተዋል።

በዚህ ወቅት የጉባኤው ሰብሳቢ ተወካይ መላከ ምህረት መምህር ፈለገ ጥበብ አንዷለም፤ አሻባሪው ቡድን በታሪካዊው የጨጨሆ መድሃኔ አለም ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰብአዊ ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን አረጋግጠዋል።

ወራሪውን ሃይል ከያዛቸው አካባቢዎች ለማስለቀቅ ለሃገራችው ክብር ሲሉ የተዋደቁና የተሰዉ ወገኖች ቤተሰቦች ያሉበትን ሁኔታ በማየት ድጋፍ ለመስጠት ጭምር በስፍራው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪውን እስከ መጨረሻው ድረስ በመደምሰስ ሀገራችን አሁን ከገባችበት የሰላም እጦት ነጻ ለማድረግ እየተካሄደ ያለውን ትግል በመደገፍ ለማበረታትም ነው ብለዋል።

ሰፊ ታሪክ ባለው የጨጨሆ መድሃኔ አለም ቤተ ክርስቲያን ላይ አሸባሪው ቡድን ባካሄደው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ታሪክን ለማጥፋት መሆኑ እንዳሳዘናቸው በመግለጽ ድርጊቱን አውግዘዋል።

ይህ ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን የዚህ አካባቢ ሃብትና ጸጋ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን በመሆኑ በተባበረ ክንድ ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል ተግባር እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

የጉባኤው  ምክትል ሰብሳቢ ሸህ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው፤ በማንኛውም የጦርነት ጊዜ ተፋላሚዎች የሃይማኖት ተቋማትንና ቅርሶችን ከአደጋ የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው ብለዋል።

መስጊዶች፣ አብያተ ክርስትያናትና ገዳማት በማንኛውም ጊዜ በኢትዮጵያውያን እሴት መሰረት ልንጠብቃቸውና ልንከባከባቸው ይገባል እንጂ ጉዳት ማድረስ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ሊወገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጥፋት ቡድኑ በቅርሶችና አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጉዳት በማድረስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያጠፋው በማስመሰል በሀገራችን ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ያለመ የተለመደ ድርጊት መሆኑን ህብረተሰቡ መገንዘብ አለበት ብለዋል።

አሁን ላይ አሸባሪ ቡድኑ በፈጸመው እኩይ ድርጊት በአለም ህግ ይጠየቃል ብለን ዝም ከማለት ይልቅ ይህን የጥፋት ሃይል ተባብረን  ማስወገድ አለብን።

“አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት በቤተ እምነቶች ላይ ሊቀጥል ይችላል” ያሉት ሸህ ሰይድ አማኞች በተደራጀ አግባብ በመንቀሳቀስ ቤተ እምነቶች እንዲጠብቁና ጉዳት የደረሰባቸውን በጋራ እንዲጠግኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በቅርስ ላይ እንደዚህ ዓይነት ውድመት የሚያደርሱ አካላትን በጋራ ማውገዝ ተመሳሳይ ጥፋት በቀጣይ እንዳይከሰት አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ የጉባኤው  ዋና ጸሃፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ ናቸው።

በምናመልክባቸውና በምንጸልይባቸው ቤተ እምነቶች ላይ ውድመት በማድረስ ትንኮሳ መፈጸም ተገቢነት የሌለው ድርጊት በመሆኑ አሸባሪው ቡድን ከሚፈጽመው አስከፊ ድርጊት ሊታቀብ ይገባል ብለዋል።

ድርጊቱ የህዝቡን ስሜት የሚጎዳው ቢሆንም አንድነቱን በዘላቂነት አጠናክሮ የላቀ ስራ ለመስራት ይነሳሳል ነው ያሉት።

የደቡብ ጎንደር  ዞን ሃገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ በበኩላቸው፤  አሸባሪ ቡድኑ በጨከነ ልቦናው  ታሪክ ባለው የጨጨሆ መድሃኔ አለም ቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት ማድረሱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የጋሳይ መድሃኒአለም ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በሃገረ ስብከቱ ስር የሚገኙ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት ማድረሱን አስታውቀዋል።

ጉዳት የደረሰባቸውን አብያተ ክርስቲያናት ለመደገፍ ለሚጥሩ ሁሉ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት አመራሮች አብያተ ክርስቲያናቱን በመጠገንና በመገንባት ሂደት መላውን ህዝብ እንዲያስተባበሩም  ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም