በአማራ ክልል በ10 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ ዘር እየተባዛ ነው

747

ባህር ዳር ፣ ነሐሴ 28/ 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በመኽር ወቅቱ በ10 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች ዘር ብዜት እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ አግደው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘር ብዜቱ እየተከናወነ ያለው በቀጣይ የምርት ዘመን ለአገልግሎት እንዲውል ነው።

የዘር ብዜት ስራው በአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ በባለሃብቶች፣ በዩኒየኖች፣ በኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽንና በፓዮኔር ካምፓኒ አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘር ብዜቱ በበቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ ቢራ ገብስ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾና ሰሊጥ ሰብሎች ላይ እየተካሄደ መሆኑን አመልከተዋል ።

በምርት ወቅቱ እየተባዛ ካለው ዘር 252 ሺህ 758 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል ።

የአባሎ ኢንተርፕራይዝ ምርምርና ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻለ አድጎ በበኩላቸው ድርጅቱ በ245 ሄክታር መሬት በቆሎና የስንዴ ዘር እያባዛ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም የመስራች ዘር እጥረትን ለማቃለል በአምስት ሄክታር መሬት የበቆሎ መስራች ዘር እያባዛ መሆኑን አመልክተዋል።

ድርጅቱ በየዓመቱ በራሱና በግለሰብ አርሶ አደሮች ማሳ ከሚያባዛው ምርጥ ዘር እስከ 6ሺህ 500 ኩንታል ዘር ለአርሶ አደሮች እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።

በብዜት ላይ ካለው በቆሎና ስንዴ 8 ሺህ 700 ኩንታል ዘር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በ2013/14 ምርት ዘመን መኽር ወቅት ከ4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል እየለማ ስለመሆኑ የቢሮው መረጃ ያመለክታል።