ለህልውናው ዘመቻ የሃይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

66

ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 28/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን የህውሃት ወራሪ ኃይል  ለመመከት እየተደረገ ባለው የህልውና ዘመቻ የሃይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

የሃይማኖት ተቋማት አመራሮችና  አባቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባሀር ዳር ከተማ እየተወያዩ ነው።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት፤ የህውሃት አሸባሪ ቡድን ህዝብ እንደ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖቱንም ለማዋረድ በጭካኔ እየሰራ ይገኛል።

ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የእምነት ተቋማትን እያወደመ  የጦር ካምፕ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የጨጨሆ መድሃኒአለም ላይ ያደረሰው ውድመት የእምነት ተቋማትን ለማጥፋት ያለውን የፀና ፍላጎት ያሳየ ነው ብለዋል።

ህዝቡንና ሃይማኖቱን አዋርዶ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አቅዶ የተነሳውን ወራሪ ለመመከትና ከገባባቸው አካባቢዎች እንዳይወጣ እየተደረገ  ባለው የህልውና ዘመቻ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማበረታታት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አሁን ላይ እየተደረገ ባለው የህልውና ዘመቻ ህዝብ በግለት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶች በፀሎትና በምህላ ተጋድሎ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካበቢዎች እየፈጸማቸው ያለው  ዘረፋ፣ የንፁሃን ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና መሰል አሰቃቂ ወንጀሎችን በአጭር ለማስቀረት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ድሉን በፍጥነት ለማብሰር የሃይማኖት አባቶች የህዝብ ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው በሃብት አሰባሰቡም ሆነ ሰራዊቱን በሰው ሃይል ለማጠናከር በማነሳሳት እንዲያግዙም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውይይት መድረኩ  የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊዎችና የሃይማኖት አባቶች ፣የፌደራልና ክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም