በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዳግም መዋቀር እንዳለበት ያመላከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዳግም መዋቀር እንዳለበት ያመላከተ ነው

አዲስ አበባ ፣ነሀሴ 28/2013(ኢዜአ) በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዳግም መዋቀር እንዳለበት ያመላከተ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ የማበረታቻ እና የእውቅና ፕሮግራም በታላቁ ቤተመንግስት ተካሂዷል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመድረኩ ተገኝተው ለአትሌቶች ሽልማቱን በመስጠት መልእክትም አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቷ በመልእክታቸው ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ የአፍሪካ ፋና ወጊ እና ታላቅ ታሪክ ያላት መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ታሪኳንና ክብሯን አስጠብቃ እንድትዘልቅ በመንግስት በኩል ለኦሊምፒክ ቡድኑ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
ሆኖም በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት መንግስትና ህዝብ የሚጠብቀውን ያክል አይደለም ብለዋል ፕሬዝዳንቷ።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት ከባለፉት 13 ኦሊምፒኮች ለኢትዮጵያ ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ውጤቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዳግም መዋቀር እንዳለባቸው ያመላከተ ሆኗል ነው ያሉት።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበውን ዝቅተኛ ውጤት በተመለከተ የሚመለከተው አካል በጥልቀት ማየት አለበት ብለዋል ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ በቶኪዮ የኢትዮጵያ ህዝብ የጠበቀውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም ብለዋል።

በመድረኩ ጎልተው የወጡ አትሌቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያን ሁሌም ከፍ ለማድረግ የሚሰራ እራሱ ከፍ ይላል ነው ያሉት።
በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ለአገሩ ወርቅ ላስገኘው አትሌት ሰለሞን ባረጋ የ3 ሚሊዮን ብር መኪና እና 40 ግራም የወርቅ ኒሻን ሽልማት ተበርክቶለታል።
በ3 ሺህ መሰናክል ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊየ ያመጣው አትሌት ለሜቻ ግርማ ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተሸልሟል።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ10 ሺህ ሜትር 3ኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ እና በ5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያመጣችው ጉዳፍ ጸጋዬ እያንዳንዳቸውን መንግስት 1 ሚሊዮን ብር ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
በውድድር መድረኩ አራተኛ በመውጣት ዲፕሎማ ያመጡ አትሌቶች እያንዳንዳቸው 200 ሺህ ብር እና ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ደግሞ እያንዳንዳቸው 150 ሺህ ብር ተሸልመዋል።
በተመዘገበው ውጤት ትልቅ ሚና የነበራቸው አሰልጣኞችም እንደየውጤታቸው እስከ 300 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሌሎች አትሌቶችና አሰልጣኞችም እንደየደረጃቸው ውጤታቸው የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል።
በቶኪዮ 2020 በእግር ኳስ ዳኝነት ኢትዮጵያን የወከለው ባምላክ ተሰማ ልዩ ተሸላሚ በመሆን 100 ሺህ ብር ተበርክቶለታል።