አሸባሪው ህወሓት በሃይማኖት ተቋማትና በንጹሀን ላይ እያደረሰ ያለው ጥቃት የሚወገዝና ሊቆም የሚገባው ነው

292

ደሴ፣  ነሀሴ 28/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወ ሓ ት በእምነት ተቋማትና በንጹሀን ላይ የፈጸመው ጥቃት የሚወገዝና በአስቸኳይ መቆም ያለበት ነው ሲል የደቡብ ወሎ ዞን የሃይማኖት ፎረም አሳሰበ።

ፎረሙ አሸባሪው ህወሓት እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጥፋት አውግዞ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤትና የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀ ህሩያን ጹመ ልሳን ገብሩ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳት እንኳ ያለ አግባብ ሊሞቱ አይገባም ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ህወሓት ግን ከኢትዮጵያውያን ባህልና እሴት ያፈነገጠ፤ በዓለም ያልታየ ግፍና መከራ በንጹሀን ላይ እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

የህወሓ ት እኩይ ተግባር በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ መሆኑን ገልፀዋል።

አሸባሪው ህዝብ በሚገለገልባቸው የእምነት ተቋማት ላይ ሆን ብሎ ጥቃት ማድረሱ እንዳሳዘናቸው ጠቁመው፤ቡድኑ ከአስነዋሪ ተግባሩ እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡

“በጦርነቱ እየደረሰ ያለውን የንጹሀን ሞት ለማስቆም ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት” ያሉት ሊቀ ህሩያን ጹመ ልሳን፣ “በንጹሃንና በእምነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተቀባይነት የለውም፤ መቆም አለበት” ብለዋል። 

ህወሓት  በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ሁሉም ተረባርቦ ከማስቆም ባለፈ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት ማስጠበቅ እንዳለበት መክረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን እስልምና ምክር ቤት ሰብሳቢ ሸህ አወል ኢብራሒም በበኩላቸው “አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ በእምነት ውስጥ ጣልቃ በመግባት እምነታችንን ሲበርዝ የኖረ የክፋት መልዕክተኛ ነው” ብለዋል።

ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ የፈጸመው በደል አልበቃው ብሎ አሁንም የእምነት ተቋማትን በከባድ መሳሪያ ማጥቃትና ማጥፋቱ ተቀባይነት የሌለው የአረመኔ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ህወሓት ከዚህ የጥፋት ተግባሩ በአስቸኳይ ሊታረም እንደሚገባ ጠቁመው፣ “ከዓለም የጦርነት ህግ ባፈነገጠ መልኩ ንጹሃንን መጨፍጨፍ፣ ቤት ማቃጠል፣ እንስሳትን ማረድና ህዝቡን አፈናቅሎ ለችግር መዳረጉ የሚወገዝ ነው” ብለዋል፡፡

“አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ያለው ጥፋት አስደንጋጭ፣ አስፈሪና ጥቁር የታሪክ ጠባሳ የሚጥል በመሆኑ በአስቸኳይ መታረም አለበት” ያሉት ደግሞ በመካነኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ተወካይ ቄስ ሙሉጌታ አለሙ ናቸው፡፡

በየትኛውም ወገን ንጹሃንን መግደል፣ ማፈናቀልና ማሰቃየት ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፤ “የእምነት ተቋማትን ማውደም በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው አስነዋሪ ተግባር ነው፤ እናወግዘዋለን” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ በጸሎትና የሚችለውን በማድረግ ይህ ክፉ ቀን እንዲያልፍ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

“ህወሓት ከኢትዮጵያውያን አብራክ የወጣ የማይመስል፣ ለሰው ርህራሄና ምንም አይነት እምነት የሌለው መሆኑን በተግባር እያየን ነው” ያሉት ቄስ ሙሉጌታ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ንጹሀንን፣ አካባቢውንና ቤተ እምነቶችን ከጥፋት እንዲታደግ ጥሪ አቅርበዋል።