ኢትዮጵያዊያን እያለን አሸባሪው ህወሓት እንጂ አገር አትፈርስም – ዘማቹ ረዳት ፕሮፌሰር

294

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 28/2013(ኢዜአ) የሕልውና ዘመቻ ጥሪውን ተቀብለው በግንባር የሚገኙት ረዳት ፕሮፌሰር ጌትነት አልማው “እኛ ኢትዮጵያዊያን እያለን አሸባሪው ቡድን እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም” ይላሉ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ጌትነት አልማው የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለመደምሰስ የቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው በማይፀብሪ ግንባር ተሰልፈዋል።

ለአገር ሉዓላዊነት መከበር ኢትዮጵያዊ ሁሉ መታገል አለበት የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ “በግንባሩ እየተፋለምኩ ያለሁት የአገሬን ሉዓላዊነት ለማስከበር ነው” ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተሰለፉበት ግንባር የመከላከያ ሠራዊቱ፣ የፀጥታ ሃይሎችና የአካባቢው ሕዝብ በጠላት ላይ ድል እየተቀዳጁ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

መላው ሕዝብ በድል አድራጊነት መንፈስ ለአገር ሉዓላዊነትና አንድነት በመዋደቅ ለግለሰቦች ስልጣን ሲል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን የህወሓት የሽብር ቡድን በያለበት መታገል እንዳለበት አመልክተዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ጌትነት “እኛ ኢትዮጵያዊያን እያለን አሸባሪው ቡድን ይፈርሳል እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ይህም በተግባር እየታየ ነው” ብለዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሚነዛውን የሐሰት ወሬ ባለመስማት የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል እያደረገ እንደሆነ መታወቅ አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

ሁሉም ዜጋ ባለው አቅም በግንባር በመገኘት፣ ባለበት ደጀን በመሆን ለአገሩ ነፃነት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማት፣ ቤተ-እምነቶችን እና የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን እያወደመና እየዘረፈ ነውም ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ።

ምንም የማያውቁ ህፃናትን ለጦርነት እያሰለፈ ለሞት እየዳረጋቸው እንደሆነም አክለዋል።