ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ችግሮችን ለመፍታት ገንቢ ሚና እንደሚኖራቸው ኢትዮጵያ ታምናለች

455

ነሐሴ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሆነው የተሾሙት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በምስራቅ አፍሪካ ችግሮችን ለመፍታት ገንቢ ሚና እንደሚኖራቸው ኢትዮጵያ ታምናለች” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደር ዲና በሳምንቱ የኢትዮጵያ አበይት የዲፕሎማሲ ክንውኖች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሆነው ባለፈው ሳምንት የተሾሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ተገቢ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በሳልና አንጋፋ የአፍሪካ ዲፕሎማት ናቸው፤ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ እንዲያገኙ ፅኑ አቋም አላቸው፤ ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ አክብሮት አላቸው ብለዋል” ቃል አቀባዩ።

በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ገንቢ ሚና ይጫወታሉ ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምንና ሹመቱን በደስታ እንደምትቀበለውም አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘግይቶም ቢሆን አሸባሪው ህወሃት እየፈጸመ ያለውን እኩይ ተግባር እየተረዳ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በቡድኑ ላይ አሁን እየቀረበ ያለውን ወቀሳና ውግዘት የኢትዮጵያ መንግሥት ቀድሞ ሲለው የነበረ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ እየፈጸመ ያለውን ጥፋት ማውገዝና የአሸባሪውን ትክክለኛ ምስል መያዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን እንደሚያጠናክር ገልጸው፤ “አንዳንዶች ያለአግባብ መንግሥትን በእርዳታ ማስተጓጎል መውቀስ የለባቸውም” ብለዋል።

ከኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳይ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ አሁንም ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።

ከሰሞኑ ሱዳን በኢትዮጵያ መሬት ላይ ድልድይ መገንባትን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትንም እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርጊቱ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

“የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ጉዳይ እናሸማግላችሁ ለሚሉ አገራት ጥረታችሁን እናደንቃለን፤ ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት አደራዳሪ አያስፈልግም፤ ሁለቱ አገራት የድንበር ጉዳዩን መፍታት የሚችሉት አገራቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በተፈራረሙት ስምምነት መሰረት ነው” ብለዋል።

ከኤምባሲዎችና ከአምባሳደሮች ጋር በተገናኘም “ኢትዮጵያ ኤምባሲ እየዘጋች ሳይሆን ኤምባሲዎች ትክክለኛ ቁመና እንዲይዙና ኢትዮጵያን የሚመጥን አቅም እንዲኖራቸው እያደረገች ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአንድ አገር ያላትን ኤምባሲ ዘጋች ማለት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አቋረጠች ተብሎ የሚነገረው ሐሳብ ነገሩን በትክክል ካለመረዳት የሚመነጭ እንደሆነ አመልክተዋል።

“ኤምባሲና አምባሳደር ሳይኖር ከዚያ አገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ እንደሚቻል ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያሳያል” ያሉት አምባሳደሩ፤ አንድ አምባሳደር በአገሩ ሆኖ የሚሰራበት (ላፕቶፕ አምባሳደር) አሰራር እንዳለም አንስተዋል።

“ሚኒስቴሩ የሚያደርጋቸው ማሻሻያዎች ሲጠናቀቁ አሁን ላሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል” ብለዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ባለፈው ሳምንት ከሳዑዲ አረቢያ፣ ታንዛንያ እና የመን 2 ሺህ 178 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አመልክተዋል።

መንግሥት ለዜጎች መብትና ክብር ትኩረት ይሰጣል፤ በተለያዩ አገራት ያሉ ዜጎቹንም ይመልሳል  ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በሳዑዲ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመመለስ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።