በዋና ዋና ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴዎች ባለፉት አስር ወራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

94

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ወራት በዋና ዋና ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ወቅታዊ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ የትክክለኛ የፖለሲ ማሻሻያ በማድረጉ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

የፖሊሲ ማሻሻያዎቹም የማይክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለማምጣት በሚያስችሉና የአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የተገኙትም ውጤቶች አገሪቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝ ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሮዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ተቋቁሞ የተገኘ መሆኑን ገልጸው ቀጣይነት ያለው ነው ብለዋል።

በዚህም በግብርናው ዘርፍ ዓመታዊ እድገቱ 5 ነጥብ 5 በመቶ ማደግ እንደቻለና በተለይም በበጋ ወቅት የመስኖ ሥራ የ220 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።  

የማዕድን ዘርፍ በተለይም የወርቅ የውጭ ንግድ እድገትም 23 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን ጠቁመዋል።

በፋይናስ ዘርፉም እድገት መመዝገቡን ጠቁመው የልማት ባንክና የንግድ ባንክ ትርፍ 22 በመቶ እንዲሁም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትርፍ 16 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል።  

በተመሳሳይ የተቀማጭ ገንዘብ 13 በመቶ እንዲሁም ብድር ምጣኔ አቅርቦት በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

የወጭ ንግድ በዘንድሮ ዓመት 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በማስመዝገብ ከባለፈው ዓመት 19 በመቶ ብልጫ ማስመዘግቡን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዓመታዊ ገቢ ላይ 600 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ መገኘቱን ጠቅሰው ይህም ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የብድር ጫናን ለማቃለል መንግሥት አነስተኛ ወለድ ያለውና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር መጠቀሙ አሁን ላይ ጫናው እንዲቀንስ አድርጓል ነው ያሉት።

በተለይም የብድር መጠኑ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ጋር ሲነጻጸር አሁን ላይ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። 

ለአብነትም የሰኔ ወር ብድር ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት አንጻር 50 በመቶ እንደነበር ገልጸው፤ ይህም ከሁለት ዓመት በፊት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል። 

አገሪቱ ብድር ለመክፈል የምታወጣው የገንዘብ መጠንም ከውጭ ንግድና ከገቢ አንጻር ሲታይ ከ2 እስከ 3 በመቶ ዝቅ እያለ መምጣቱን አስረድተዋል።

በተጓዳኝም አገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸውን የዘይትና የስንዴ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት መንግሥት ከግል ዘርፉ ጋር በመሆን ከፍተኛ ርብረብ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የዘርፉን አሰራር ከማሻሻል ጀምሮ ከፍተኛ የማበረታቻ ሥልቶች ተቀይሰው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸው፤በዚህም ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

አገሪቱ አሁን ከገጠማት የህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ ሊመጡ የሚችሉ አሉታዊ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ መፍትሄዎች መቀየሳቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም