ሰላም ማስከበር ግዳጆች እንዲሳኩ አገራት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው

312

አዲስ አበባ፣  ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ)  ዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ግዳጆች እንዲሳኩ አገራት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቆመ።

ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሰራዊት የሚያዋጡ አገራት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ ሲመክሩ ቆይተው ምክክሩ ዛሬ ተጠናቋል።            

ምክክሩ ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን፤ ዓላማውም እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በተያዘው ዓመት ማገባደጃ ላይ ደቡብ ኮሪያ ሲኦል ከተማ ሰራዊት የሚያዋጡ አገራት ሚኒስትሮች ለሚያደርጉት ጉባኤ ግብዓት ለማሰባሰብ ነው።        

በኢትዮጵያ የተካሄደው ይሄው መድረክም ኢትዮጵያ፣ ጃፓንና ኢንዶኖዥያ አገራት በጋራ ያዘጋጁት  ነው።          

በዚሁ መሰረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ምን ያስፈልጋል? አገራት እንዴት በቅንጅት መስራት አለባቸው የሚለው ተዳሶበታል።            

በሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም አዛዠ ብርጋዲዬር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ እንደተናገሩት፤ በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበሩ ረገድ ያላት ሚና ማንጸባረቅ ተችሏል።  

ጉባኤው ስኬታማ እንደነበር ያስታወሱት ብርጋዲዬር ጄኔራል ሰብስቤ፤ ሠላም ማስከበሩ ላይ ያሉ ችግሮች የተለዩበት እንደሆነም አብራርተዋል።    

“ሠላም ማስከበር የአንድ አገር ብቻ ስራ መሆን የለበትም” ያሉት አዛዡ፤ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ለግዳጅ አፈጻጸሙ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።      

በተለይም ያደጉት አገራት በአቅም ግንባታ ዙሪያ የሚሰጡት ድጋፍ የሰላም አስከባሪዎችን ፍላጎት ያሟላ በመሆን ረገድ ክፍተት እንዳለበት ነው የጠቆሙት።    

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚሰጡ ስልጠናዎች የሚገጥሙ ችግሮችን ተከታትሎ መለየትና መደገፍ እጥረት መኖሩ በጉባኤው መነሳቱን አብራርተዋል።        

ከቴክኖሎጂ አኳያም ያደጉት አገራት በቴክኖሎጂ ስልጠና እንዲሰጡ እና ሰላም አስከባሪዎች የቋንቋ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባም አክለዋል።