በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመግታት የተቀናጀ ጥረት መደረግ እንዳለበት ተመለከተ

261

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ)በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እንዲያግዝ ክትባት ከመውሰዱ በተጓዳኝ መሰረታዊ የመከላከያ መንገዶች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተመለከተ።

በክልሉ እስካሁን 300 ሺህ ሰዎች ክትባት ወስደዋል።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የ2013 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀምና ቀጣይ  የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ አካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤  በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ቢሆንም፤በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው መዘናጋት አሳሳቢ ነው።

ወረርሽኙን ለመከላከል ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ቅድሚያ በመስጠት በመጀመሪያው ዙር  ለ300 ሺህ ሰዎች ክትባት መሰጠቱን ገልጸው፤ የሁለተኛ ዙርም መቀጠሉን  አስረድተዋል።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣውን ወረርሽኝ ለመከላከል መሰረታዊ የመከላከያ መንገዶች ተብለው የተለዩ  የጭምብል አጠቃቀም፣ የመራራቅና የንፅህና አጠባበቅ ዘዴዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዴልታ የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ዝርያ ለመከላከል ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በቢሮው የእናቶናን ሕፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት የክትባት ከፍተኛ ባለሙያና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ዐቢይ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃኑ በቀለ ፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን መደበኛ የጤና አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተለይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከላትን አንድ ብቻ ከነበረበት ወደ ሰባት በማሳደግ 200 ሺህ ለሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ምርመራ መደረጉን  ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከተመረመሩ ወስጥ 8 ሺህ 690 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ጠቅሰው፤ 147 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ200 ሺህ በላይ ሕዝብ ለመከተብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀላባ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ዞኑ በክልሉ መጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ የተገኘበት እንደሆነ አስታወሰው፤ በወቅቱ በህብረተሰቡ ውስጥ የነበረው ጥንቃቄ መልካም በመሆኑ  አስከፊ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ችለናል ብለዋል።

አሁን ላይ እየተስተዋለ ባለው መዘናጋት ሥርጭቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚጠቁሙ ማሳያዎች እንዳሉና ከሶስተኛው የወረርሽኙ ማዕበል ክስተት ጋር ተያይዞ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዞኑ ቀደም ሲል አንድ በመቶ የማይበልጠው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች መጠን አሁን ከሰባት በመቶ በላይ መድረሱን ኃላፊው አመልክተዋል።