በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የገጠመው የግብዓት እጥረትና የሃይል አቅርቦት ችግር እልባት እንዲሰጠው ተጠየቀ

689

አዲስ አበባ፣  ነሃሴ 27/2013(ኢዜአ) በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የገጠመው የግብዓት እጥረትና የሃይል አቅርቦት ችግር በአስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጠየቀ።

በተለያዩ ችግሮች የተዘጉ የጣፋጭ ምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል::

በኢትዮጵያ በስኳርና ጣፋጭ ምግቦች አምራች ዘርፍ ያሉ 153 ፋብሪካዎች ለ20 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።

የንግድ ሚኒስቴር በቅርቡ ባደረገው ጥናት መሰረት በተደራራቢ ታክስ፣ በግብዓት እጥረትና በሃይል አቅርቦት ችግር ዘርፉ እየተፈተነ ይገኛል።

በስኳርና ጣፋጭ ምግቦች አምራች ዘርፍ ካሉ ፋብሪካዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በተጠቀሱት ችግሮች ማምረት አቁመዋል።

አምራቾቹ በግብዓትነት ከሚጠቀሙት ስኳር 35 በመቶ ቫትና ኤክሳይዝ ታክስ፣ ምርታቸውን አምርተው ሲሸጡ 15 በመቶና 20 በመቶ ኤክሳይዝ በድምሩ 70 በመቶ ተደራራቢ ታክስ ተጥሎባቸዋል።

በዚህም ምክንያት ዘርፉ ለተጨማሪ ችግር በመዳረጉ የሚያስተዳድሯቸውን ሰራተኞች ከመበተን ባለፈ መንግስትን ገቢ እያሳጣው መሆኑን የሚኒስቴሩ ጥናት አመላክቷል።

የንግድና ኢንዱሰትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ተካ ገብረኢየሱስ፤ ኢንዱስትሪዎቹን መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት በባለድርሻ አካላት አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልጋል ብለዋል።

በ2012 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገው የኤክሳይዝ ታክስ በዘርፉ ላይ የጣለው ተደራራቢ ታክስ የዘርፉ ቀዳሚ ችግር መሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል።

በዚህም ሳቢያ አምራቾቹ ያለቀለት ምርትን ከውጭ አምጥተው ከሚሸጡት ጋር ተወዳዳሪ መሆን አለመቻላቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

በዚህም ሳቢያ መንግስት ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት ፈጥሯልም ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የስኳር ኮርፖሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

የሚሰጣቸውን የስኳር ኮታ ላልተገባ ዓላማ የሚያውሉ አምራቾች ላይ የኢትዮጵያ ስኳርና ጣፋጭ ምግብ ማህበር ክትትል እንዲያደርግም ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።

በአገሪቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ችግሮቻቸውን በጥናት በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ስኳርና ጣፋጭ ምግብ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤልያስ ተሾመ፤ በጥናት ባልተመሰረተ ታክስ ሳቢያ የዘርፉን ተዋናዮች ለጉዳት ዳርጓል ብለዋል።

በግብር ከፋይነታቸው ታማኝ ተብለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሸለሙ የዘርፉ ተዋናዮች በተደራራቢ ታክስ ሳቢያ ስራቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል ባለድርሻ አካላትን በማወያየት በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ እንዲሰጥና የግብዓት እጥረቱን በአፋጣኝ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር እና የስኳር ኮርፖሬሽን ተወካዮች፤ የዘርፉን ችግር ተመልክተው በጥናት የተደገፈ ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።