ኮሚሽኑ የአካባቢ ብክለትና ተያያዥ መረጃዎችን የያዘ አዲስ ድረ-ገፅ አስተዋወቀ

77

አዲስ አበባ ፣ነሀሴ 27/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት፣ የላቦራቶሪና ናሙና ውጤቶች፣ የአየር ብክለት መጠን ልኬትና የተጠኑ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መረጃዎችን የሚያሳይ አዲስ ድረ-ገፅ አስተዋወቀ።

ከነገ ነሐሴ 28 ቀን 2013 ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጠው የኮሚሽኑ ድረ-ገፅ መረጃዎች በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግሪኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በዓረብኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በደች ቋንቋዎች ይቀርባሉ።

በድረ-ገፁ የአካባቢ ብክለት መረጃ፣ የዘርፉ የላቦራቶሪና ናሙና ውጤቶች፣ የዕለት ተዕለት የአየር ብክለት መጠን ልኬትና የተጠኑ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማዎችን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎች የሚካተቱ ይሆናል።

ምክትል ኮሚሽነር ዋለልኝ ደሳለኝ ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ስለ አካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን መረጃ ባሉበት ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።

ይህም ኮሚሽኑ መረጃዎችን በበራሪ ወረቀቶች ለማዳረስና በአካል በመገኘት ለመስጠት የሚፈጀውን ጊዜ እንደሚቆጥብ ተናግረዋል።

ድረ-ገፁ ተቋሙ በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚለቃቸው መረጃዎች የተሻለ ተዓማኒነት እንደሚኖረውና የተብራራ መረጃ እንደሚካተትበት ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ አሻግሬ በበኩላቸው ድረ-ገፁ መረጃን ያለገደብ ለማድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የተቋሙ ሠራተኞችና የውጭ ተገልጋዮችም ወቅቱን በሚመጥንና ዘመኑ በሚከተለው ቴክኖሎጂ የሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ ያግዛል ነው ያሉት።

ድረ-ገፁ የተገልጋዮችን ቅሬታ፣ አስተያየትና ጥቆማ ለመቀበል አመቺ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ድረ-ገፁ ተግባር ላይ ከዋለም በኋላ እየተሻሻለና መረጃዎቹም በየጊዜው እየታደሱ የሚቀርቡበትና ለተገልጋዮች ወቅታዊ መረጃ የሚደርስበት እንደሚሆን አክለዋል። 

ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻርም የሥራ ማስታወቂያ፣ ስለ ተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች የቅሬታና የአስተያየት መስጫ ሳጥንም ተካተውበታል።

የድረ-ገፁ ተሞክሮ የተወሰደው ከአሜሪካ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ባለሥልጣን ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም