ህዝቡ ለሀገሩ ወታደር መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው

99

ሰመራ ፤ ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ) ወንድ ሴት ፤ ትልቅ ትንሽ ሳይል በዚህ ወሳኝ ወቅት የአፋር ክልል ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለሀገሩ ወታደር መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባዔ ሲጠናቀቅ እንዳመለከቱት፤ አሸባሪው ህወሃት ባለፉት ዓመታት እንደ መንግስት ሀገሪቱን ባስተዳደረበት ወቅት የሀሰት ፌዴራሊዝም ስርዓት ዘርግቶ በክልሉ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በደል ሲፈጽም ቆይቷል።

ይሁንና ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ውስጥ የነበረው ኢ-ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና ማጣቱን ገልጸዋል። 

ይህንን ያጣው ቡድኑ በክልሉ የፈጸመው ወረራ እንደቀድሞ በእጅ አዙር የማስተዳደር ፍላጎት ያነገበ፤ ካልተሳካለትም የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ትራንስፖርት መስመርን በመቆጣጠር ሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ መጣል ነው ብለዋል። 

የጥፋት ዓላማውን ለማሳካት የራሳችንን ሰዎች ቁልፍ የመጫዋቻ ካርታ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤ ከአሸባሪው ጋር ሆነው በወገኖቻቸው ላይ ጦር ያነሱ ሰዎች ዋነኛ ጠላታችን መሆናቸውን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል ነው ያሉት።


የአሸባሪውን እኩይ ዓላማ በእንጭጩ ለማስቀረት ጦርነቱን የሀገር ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ወንድ ሴት፤ ትልቅ ትንሽ ሳይል በዚህ ወሳኝ ወቅት የአፋር ክልል ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለሀገሩ ወታደር መሆኑን በተግባር እያሳየ መሆኑን አቶ አወል ተናግረዋል። 

በዚህም ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት አሸባሪውን በጀግንነት በመፋለም አኩሪ ጀብዱ ፈጽሟል ብለዋል።


አሸባሪው የህወሃት ቡድን ባደራጃቸው የዲጂታል ወያኔና ቅጥረኞቹ አማካኝነት የሚነዛው የሀሰት ወሬ ህብረተሰቡ እየተረዳ በመምጣቱ ሴራው እንደከሸፈበት ገልጸዋል።

ሕዝቡ ባንዳዎችን አሳልፎ እንዲሰጥና ቡድኑ የሚያሰራጨውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ችላ በማለት ህልውናውን ለማስከበር መትጋቱን እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ጦርነቱን ለመቀልበስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ርዕስ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ከዚህ ሻገር በዲፕሎማሲያዊ መስክም የ”ጋሊኮማው”ን ጭፍጨፋን ጨምሮ በንጹሃን አፋር አርብቶ አደሮች ላይ የፈጸመውን የግፍ ግድያ ለአለም አቀፉ ማህበረሰቡ በማጋለጥ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።


በዚህም እውነታውን ማወቅ የሚፈልጉ የአለም አቀፉ ሰብአዊ ድርጅቶችና የተለያዩ የአለም ሀገራት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ።


በዚህ ረገድ የዲያስፖራው ማህበረሰብ የአሸባሪውን እኩይ ሴራ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማጋለጥ ባሻገር ተጎጂ ወገኖችን በገንዘባቸውና እውቀታቸው በመደገፍ እስካሁን ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም በተለይም በዲፕሎማሲው መስክ ተሳትፏቸዉ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።


የምክር ቤቱ አባል አቶ ጀማል መሐመድ በበኩላቸው፤  የአሸባሪው ህወሃት ሴራ ለማክሸፍ  የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ትናንት በክልሉ የፈጸመውን ብዝበዛና መረን የለቀቀ ጣልቃ ገብነት አልበቃ ብሎት ዛሬ በጉልበት ሊገዛን የተነሳውን ቡድን አንታገሰውም ብለዋል።

አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ሕዝብ ላይ  ወረራ በማካሄድ ግድያ፣ ዘረፋና ግፍ ሲፈጽም ቀደም ሲልም ሲያደርግ የነበረው አካል እንደሆነ የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኡስማን አኔሳ ናቸው።

የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው ጠላታችንን መመከት አለብን ብለዋል።