ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ያዘጋጀችውን የመጀመሪያውን ዙር ችግኝ ለኤርትራ ላከች

433

ነሀሴ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ለመስጠት ቃል ከገባችው ችግኝ የመጀመሪያውን ዙር ለኤርትራ መላኩን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ።

በአገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቀዱ ጥሩ አፈጻጸም እንዳለውም ተመላክቷል።

የቴክኒክ ኮሚቴው አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ለመስጠት ቃል ከገባችው የ1 ቢሊዮን ችግኝ መካከል የመጀመሪያውን ዙር ለኤርትራ ተልኳል።

ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ አፍሪካን አንድ የማድረግ ሃሳብ ይዛ እንደተነሳችው ሁሉ አረንጓዴ ልማትም የአፍሪካ አጀንዳ ሆኖ በፓን አፍሪካኒዝም ማዕቀፍ ውስጥ እንዲታይ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሀሳቡን እየተቀበሉ ያሉ አገራት መኖራቸውን የጠቀሱት ዶክተር አደፍርስ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በአምባሳደሮች በኩል ከአገራቱ ጋር ሰፊ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተወሰኑ አገራት የችግኝ ቁጥር ፍላጎታቸውንና የመትከያ ጊዚያቸውን በኢትዮጵያ ቆንስላዎች በኩል መረጃ እያደረሱ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ዙር ችግኝ ትናንት ወደ ኤርትራ መጓጓዙን የገለጹት ዶክተር አደፍርስ ችግኞችን ለሌሎች አገራት የማጋራት ዓላማው በአፍሪካ ደረጃ ትብብርን ማጠናከር ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በአገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ሲተገበር ቆይቷል።

ዕቅዱ ይሳካ ዘንድም በፌዴራልና በክልሎች አስተባባሪነት ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ሲከናወን ቆይቷል።

የክልሎችን ሪፖርት ጨምሮ ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከሌሎች የተሰባሰበው መረጃ ውጤቱ ጥሩ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

“በአገሪቷ አለመረጋጋት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ዕቅዱ በሚፈለገው ልክ አልሄደም” ያሉት ዶክተር አደፍርስ ትግራይ፣ አማራና አፋር አካባቢዎች በአረንጓዴ አሻራ ትግበራው ወደኋላ እንደቀሩ ጠቁመዋል።

በሌሎች አካባቢዎች ግን በችግኝ ጣቢያዎች የፈሉ ችግኞች በአግባቡ መተከላቸውን ሪፖርቶች አመላክተዋል ብለዋል።

ለአገር በቀል ችግኝ ዝርያዎች የሚሰጠው ትኩረት እየተሻሻለ መምጣቱንና በቀጣዩ ዓመትም የበለጠ እንደሚሰራበትም ዶክተር አደፍርስ አመልክተዋል።