‘100 ብር ለወገኔ’ የሚል አገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው

280

አዲስ አበባ፣  ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ)  ‘100 ብር ለወገኔ’ የሚል አገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ሊካሄድ መሆኑን የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይልማ ተረፈ፤ ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ‘100 ብር ለወገኔ’ የተሰኘ የገቢ ማሰባሰቢያ የወጣቶች ንቅናቄ ሊካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

በንቅናቄው ከአንድ ወጣት 100 ብር በመሰብሰብ በግንባር ላይ ሃገራቸውን ከአሸባሪው ህወሓት በመከላከል ላይ ላሉ የጸጥታ አካላትና ይኸው ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ባደረሰው ጥቃት ለተፈናቀሉ ወገኖች ለመለገስ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በንቅናቄው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶችን ለማሳተፍና  180 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

አሸባሪው ህወሓት ዘመቻ የከፈተው ለመንግሥት ካለው ጥላቻ  ሳይሆን አገርን ለማፈራረስ ካለው ፍላጎት መሆኑን አቶ ይልማ ገልጸዋል።

በመሆኑም የጥፋት ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎች በንፁሃን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ አይቶ  መረዳቱንም ተናግረዋል።

በአሸባሪው የጭካኔ ተግባርም ኢትዮጵያዊያን ቁጭት አድሮባቸው ለአገራቸው ህልውና በጋራ እንዲቆሙ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ወጣቱ የአገሪቱ ዜጋ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲነሳና የቻለ የፀጥታውን መዋቅር ተቀላቅሎ እየተዋጋ፣ ያልቻለው ደግሞ ድጋፍ በማሰባሰብና አካባቢውን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሰዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሩም ይህንኑ የሚያጠናክር መሆኑን የተናገሩት አቶ ይልማ በጳጉሜ ወር ውስጥ የተሰበሰበውን ገቢ ለተፈናቃዮች የአዲስ ዓመት በዓል መዋያ ለማድረስ ነው ብለዋል።

መርሃ-ግብሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፊታችን ጳጉሜ 1 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ አሥር ቀናት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።