አገር አቀፍ የአይ ሲ ቲ ልማት ፎረም በድሬዳዋ ተጀመረ

96

ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 27/2013 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቋቋሙለትን ዓላማ ለማሳካት የሚያግዝ ሀገር አቀፍ የቢዝነስና የአይ ሲ ቲ ልማት ፎረም ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ።

ፎረሙን ያዘጋጁት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው።

የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ ፎረሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቆሙላቸውን መሠረታዊ ዓላማዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመፈፀም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

"አይ ሲ ቲ መጠቀም ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
በተለይ የመማር ማስተማር ሂደት ጥራት ለማረጋገጥና በፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሰራሮችን ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሸጋገር ተግባራትን ልምድ እንደሚቀመርበት ተናግረዋል።

ፎረሙ በ2014 የትምህርት ዘመን አይ ሲ ቲን ለማስፋፋት የተያዙ ፕሮጀክቶችን ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

በፎረሙ ከ40 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ከ350በላይ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን፣የአስተዳደርና ቢዝነስ ልማት ዳይሬክተሮችና የመስኩ ምሁራን ፣የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም