በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሴት አመራሮች ማዕከል የማድረግ እቅድ ተይዟል

84

አዲስ አበባ ነሃሴ 27/2013(ኢዜአ) በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሴት አመራሮች ማዕከል የማድረግ እቅድ ተይዟል።

የኢፌዴሪ የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ባዘጋጀው የአስር ዓመት የልማት እቅድ ላይ ለወጣቶች፣ ሴቶች እና ኢ-መደበኛ ንግድ ላይ የተሠማሩትን ላይ የሰጠውን ትኩረት በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ 
በመድረኩ ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝ ከአፍሪካ ሬኔሳንስ ቴሌቪዥን (አርትስ) ጋር በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ተቋማት ተገኝተዋል።

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፕላንና ልማት ኮሚሽን አማካሪ አቶ ደመቀ ፀሐዬ፤ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተሰናዳው የአስር ዓመቱ አገራዊ የልማት ዕቅድ ከልዩ ባህሪያቱ አንዱ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ 
በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ግብ ተደርገው ከተያዙት መካከል በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በቀጣይ የማህበራዊ ደህንነትና ዋስትና ልማት ዓላማዎችን ማሳካት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኢ-መደበኛ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን በጥናት በመለየት ወደ መደበኛ ኢኮኖሚ የሚሸጋገርበት ስልት ተቀይሶ ሥራ ላይ የማዋል ግብ ተይዟል ብለዋል፡፡ 
በመሪ የልማት ዕቅዱ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ 3 መሰረታዊ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል ብለዋል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ተፈጥሯዊ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩላቸው ማድረግ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ምጣኔ በ2008 ዓ.ም ከነበረበት 23 በመቶ በ2022 ዓ.ም ወደ 5 በመቶ ለመቀነስ መታቀዱን አብራርተዋል። 


በመሪ እቅዱ መሰረት የውክልና ተሳትፎን ማረጋገጥን በተመለከተም ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች በየደረጃው በሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲሳተፉ ይደረጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሴቶች አመራር ማዕከል በማድረግ ከአገር አልፎ ለአህጉር ብሎም ለአለም ተምሳሌት የሆኑ ብቁ ሴት አመራሮችን ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።

የአፍሪካ ሴት አመራሮች ማዕከል በመገንባት በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ ለአመራር ብቁ የሆኑ በርካታ ሴቶችን ለማፍራት መታቀዱን አማካሪው አስረድተዋል፡፡ 
በአጠቃላይ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው::

ለዚህም ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሴቶችና፣ ወጣቶችን እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች በኢ-መደበኛ ኢኮኖሚ የተሰማሩትን ጨምሮ ተሳታፊና ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም