የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበራሰብ አገልግሎቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን አከናወነ

1108

አሰላ፤ ነሐሴ 26/2013 (ኢዜአ) የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ችግርን ለመፍታት በሚያግዙ ምርምሮችና ማህበረሰብ አገልግሎቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያከናወናቸው  አገልግሎት  እንዲሁም የተያዘው የስራ ዘመን   የጥናትና ምርምር እቅዶችን ለባለድርሻ አካላት በአሰላ እያሰገመገመ ነው። 

የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዘርፍ ፕሬዚዳንት ዶክተር አደም ከዲር እንዳሉት፤ በተቋሙ ከተካሄዱት የጥናትና ምርምር ስራዎች ውስጥ 170 የሚሆኑት በህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አፈታት  ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በአካባቢው የሚታወቀውን የስንዴ፣ ገብስና ጥራ ጥሬ ሰብሎችን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝሪያዎችን ለአርሶና  አርብቶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የድህነት ቅነሳና ስራ ዕድል ፈጠራ ደግሞ የምርምር ስራዎቹ እንደሆኑ ጠቀሰዋል።

በተፈጥሮ ሀብት መመናመን አደጋ የተጋረጠባቸውን እንደ ደንበል ሃይቅ፣ ጥዮ፣ ድገሉና ቦቆጂ ተፈጥሮ ሀብት፣ በአሰላና ጭላሎ ተራራ ዙሪያ እንዲሁም በመራሮና ዝዋይ ዱግዳ ላይ የአካባቢ ጥበቃና የጥናትና ምርምር ስራዎችንም አንስተዋል።

በማህበረሰብ አገልግሎት በተለይ የገቢ ማስገኛ አማራጮች፣ጤና፣ ትምህርትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ 22 ፕሮጀክቶችን በማከናወን  ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ ማመቻቸታቸውን አስረድተዋል።

በዶሮና የወተት ላሞችም  የአካባቢውን ማህበረሰብ  ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ አቅም ለሌላቸው ነፃ የህግ አገልግሎት፣ የዓይን ሞራ ህክምናና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን መስጠቱንም ዶክተር አደም አውስተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በደጋው አካባቢ በግብርናና ሰብል ልማት ላይ ከሚሰራው ምርምር በተጨማሪ ከኦሮሚያ አርብቶ አደር ኮሚሽን ጋር በመተባበር በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳና ምዕረብ አርሲ ዞን ቆላማ ወረዳዎች የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያ ጥናት እያከናወነ ነው።

ተቋሙ ሀገር በቀል ዕውቀት እንዲስፋፋ፣ ባህልና ሳይንሱን ለማጣጣም የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን  እያከናወነ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ቃሲም ናቸው።  

በተለይም የገዳ ስርዓት፣ የሲንቄ ባህላዊ ዕርቀ ሰለም፣ የጉማና ሽማግሌዎች ሚና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከሳይንሱ ጎን ለጎን ድርሻ እንዲኖራቸው እየሰራን ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ስድስት ኮሌጆች በእናቶችና ህፃናት፣ እንዲሁም የስነ ባህሪ፣ በሰብዕናና ሌሎች መስኮች ላይም ጥናት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የጥናትና ምርምር ስራዎቹ ከአካባቢው አስተዳደር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶች ጋር በማጣጣም 50 በመቶ የሚሆኑትን ለማህበረሰብ አገልግሎት ችግር ለመፍታት እንዲያግዙ ስራ ላይ  ማዋላቸውንም አመልክተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም 134 የልማትና ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች መቀረጻቸውንም ጠቅሰዋል።

ለጥናትና ምርምር ስራዎቹ 38 ሚሊዮን ብር  ተመድቧል ነው ያሉት።

በግምገማው መድረክ  የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በሚደረጉ  ጥናቶችና ምርምሮች እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች የታዩት ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመለየት ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ እንደሚቀመጡ የኢዜአ ሪፖርተር ከአሰላ ዘግቧል።