አገራዊ ምርትን 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ በቅንጅት እየሰራ ነው.... የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር

119
አዳማ ነሀሴ 6 /2010 ዓ.ም ዋና ዋና የምግብ ሰብሎችን በእጥፍ በማሳደግ አገራዊ ምርትን 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ። የፌዴራል ግብርና ልማት አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል11ኛ መደበኛ ጉባኤው በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። በሚኒስቴሩ የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢያሱ አብርሃ እንዳሉት በአገሪቱ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ የአፈር አሲዳማነት 43 በመቶ፣ ጨዋማነት አምስት በመቶ እና የኮትቻ አፈር ደግሞ 11 በመቶ መሸፈኑ የሚፈለገው የግብርና ምርት እንዳይገኝ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በዚህ በኩል ያሉትን ዋና ዋና ተግዳሮቶች በመለየት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይ አሲዳማ አፈርን በኖራ ለማከምና ጨዋማነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከእዚህ በተጨማሪም የውሃ አጠቃቀምን በአግባቡ በመቆጣጠርና የኮትቻ አፈርን ውሃ በማጠንፈፍ ውሃውን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው። ይህም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ቀሪ ዓመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። ለምርት ዕድገት እውን መሆን ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርቱ ወደ ጎተራ እስከሚገባበት ዘመናዊ የአሠራር ዘዴዎች ተግባራዊ  በመደረግም ላይ መሆናቸውን ዶክተር ኢያሱ ገልጸዋል። በ2008 ዓ.ም በአገሪቱ ያጋጠመውን ከፍተኛ ድርቅ በመቋቋም 266 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን በ2009/2010 ምርት ዘመን 306 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን እቅድ መጨረሻም አገራዊ ምርትን 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም የበጋ መስኖ፣ የበልግና የመኸር እርሻን እንዲሁም ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በቅንጅት እተሰራ ነው፡፡ መክክር መድረኩ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር፣ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ከማስተግበር አኳያ ካውንስሉ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለበትም ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል። በሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ የኔነሽ ኤጉ በበኩላቸው የፌዴራል ግብርና ልማት አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን በመድረኩ ላይ አቅርበዋል። ዳይሬክተሯ በሪፖርቱ ላይ እንዳመለከቱት የግብርና ልማት የብዙ አካላትን ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ በየደረጃው ካውንስል በማቋቋምና በማጠናከር ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይ በግብርና ኤክስቴንሽን፣ በአፈር ለምነት ማሻሻል፣ በአነስተኛ መስኖ ልማት፣ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የዘር ብዜትና አቅርቦት ሥርአት እንዲዘረጋ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ በእጽዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር፣ በግብርና ሜካናይዜሽን፣ በመጤ አረምና ተምች መከላከልና በ10ኛው ካውንስል የተላለፉ ሌሎች ውሳኔዎችንም ለመፈጸም ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀውና ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ መድረክ ላይ ከፌዴራል፣ ከሁሉም ክልሎችና ዞኖች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም