ሽብርን ለመከላከል አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

334

ጋምቤላ፣ ነሐሴ 25 /2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የአሸባሪዎቹ የህወሓትና የሸኔ ተላላኪዎች ሽብር ለመፍጠር የሚያደርጉትን ሴራ ለማምከን አንድነትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መሰተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።

የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት የሽብር ቡድኖቹ ተላላኪዎች የክልሉን ሰላም ለማወክ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ሕዝቡና አመራሩ አንድነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል።

“የሽብር ቡድኑና ተላላኪዎቹ ባለፉት ሶስት ዓመታት የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ሲሞክሩ የቆዩ ቢሆንም በሕዝቦች አንድነትና የጋራ ጥረት ፈተናዎችን በድል መሻገር  ተችሏል” ብለዋል።

የሽብርተኞቹንና የተላላኪዎችን ተልዕኮ በማክሸፍ የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባ  አሳስበዋል።

ተላላኪዎቹ በጋምቤላ ከተማና አካባቢው ደግሰውት የነበረው ሽብር በሕዝቡና በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት መክሸፉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዋይ ጆክ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑን ተላላኪዎች እኩይ ሴራ ለማምከን ሕዝብን ያማከለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

“የክልሉ ሕዝብ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያገኘውን ሰላም ለማስጠበቅ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የሽብር ቡድኑን ተላላኪዎች ሴራ ለማምከን መሰራት አለበት” ብለዋል።

“የሽብር ቡድኑንና ተላላኪዎቹን በንቃት መከታተልና መቆጣጠር ያስፈልጋል” ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ በኮች ማሞ ናቸው።

“ወጣቱ የሽብር ቡድኖቹ ተልዕኮ አስፈጻሚ እንዳይሆን ግንዛቤውን ማሳደግ ይገባል” ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጋልዋክ ዎል ናቸው።