ጨለማ የሚመስለውን ፈተና ተሻግረን ብርሃን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም

294

ሚዛን ፤ ነሐሴ 25/2013 (ኢዜአ) አሁን ላይ ጨለማ የሚመስለውን ፈተና ተሻግረን ብርሃን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

የቤንች ሸኮ ዞን ሴቶች መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ ዛሬ ሰልፍ አካሂደዋል።

በዚሁ ወቅት የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ሀረገወይን ወልደገብርኤል እንዳሉት፤  “ግንባር ላይ ባንሰለፍም ሁላችንም ጦርነት ላይ ነን”።

ስንቅ በማዘጋጀትና አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ የደጀንነት ድጋፋቸውን በመቀጠል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ሴቶች ስንቅ ከማቅረብ ባለፈ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አክብሮትና አጋርነት ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

ሌላዋ የሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ፍርዳወቅ አለሙ፤ ለመከላከያና ሌሎች የፀጥታ አካላት ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት በሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ሊያጠፉ የተነሱት አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተደምስሰው በሀገሪቱ ሰላም እስኪሰፍን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ሴቶቹ ያስታወቁት።

በየትኛውም መንገድ ለመንግስት ጥሪ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

 የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅነሽ ባድንስ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በጦርነት የመጀመሪያው የጉዳት ሰለባ የሚሆኑት አቀመ ደካሞች  መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሀገር ላይ ጦርነት አውጀው የሽብር ተግባር እየፈጸሙ ያሉት ህወሓትና ሸኔ ከምድረ ገጽ እስኪጠፉ ድረስ የዞኑ ሴቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ኢትዮጵያውን ድሮም በሀገር ጉዳይ ተለያይተው አያውቁም፤ በተባበረ ክንድ ድል በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም እናሰፍናለን ነው ያሉት።

ለራሱ ህዝብ የማይጨነቀውን አሸባሪው ቡድን ለመደምሰስ በሚካሄደው ትግል የድርሻቸውን ለመወጣት ሴቶች በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ሴቶች ፣ህጻናት እና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ባንቻየሁ ዳዲ ናቸው።

ልጆቻቸው ዘምተው የሀገር ጠንቅ የሆኑትን አሸባሪዎች እንዲደመስሱ ከመላክ አንስቶ በገንዘብና ቁሳቁስ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዞኑ የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ታደለች መልካሙ በበኩላቸው፤ የቤንች ሸኮ ዞን ሴቶች በሁለተኛ ዙር 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ስንቅ አዘጋጅተው ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።

በሦስተኛ ዙር የስንቅ ዝግጅት 1 ሺህ 400 ኪሎ ግራም በሶ፣ ዳቦ ቆሎና ኩኪስ አዘጋጅተው ዛሬ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ እስኪደመሰሱ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ወይዘሮ ታደለች የተናገሩት።

በብልጽግና ፓርቲ የርዕዮተ ዓለም ጽህፈት ቤት የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር  ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ወልደ ትንሣኤ ፤  አሁን ላይ የጨለመ የሚመስለውን ፈተና ተሻግረን ብርሃን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል።

የማይናገሩ እንስሳትን የሚጨፈጭፍ ባንዳን በተባበረ ክንዳችን ይደመሰሳሉ፤ በፍጥነት እንዲጠፋ ልጆቻችን ዘምተዋል እኛ ስንቅና ሞራል እየለገስን ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ሴቶች ዛሬ በሚዛን አማን ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ የአሸባሪዎቹን የጥፋት ደርጊት በማውገዝ   ለመከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት በጋራ ባሰሙት ድምጽ አረጋግጠዋል።