ቀጥታ፡

ክብር ያለው ሞት ልሞትላት ሁርሶ ተገኝቻለሁ -መምህርና ምልምል ወታደር

ድሬዳዋ፣ ነሀሴ 24/ 2013 (ኢዜአ) ለሀገሩ ክብር ያለው ሞት ለመሞት በመወሰኑ በቆላማ የአየር ንብረት ነፋሻማ አየር በሚነፍስበት በሁርሶ የኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መገኘቱን  መምህርና ምልምል ወታደር ፍቃዱ አለማየሁ ይገልጻል።

በ1972 ዓ.ም. የተቋቋመው የሁርሶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ወታደራዊ መኮንኖች ጨምሮ ታላላቅ ጀብድ የሰሩ ጀግኖችን  ያፈራ ነው።

ማሰልጠኛ ተቋሙ ለሀገር ሉአላዊነትና ለዓለም  ሰላም መረጋገጥ  አበርክቷቸው  ከፍ  ያሉ  የሠራዊት አባላት የበቀሉበትም መሆኑ ይታወቃል።

ዛሬ ላይ ደግሞ አሸባሪው የህወሀት ቡድን  በከፈተው ጦርነት ሀገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመታደግ ቆርጠው የተነሱ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በምልምል ወታደርነት በማሰልጠኛ ጣቢያው ተገኝተዋል።

ትላንት ከአባቶች የተቀበሏትን ሀገር ለነገው ትውልድ ከነክብሯ ለማስረከብ  የተሰናዱ  ምልምል የሠራዊት አባላት በማነቃቂያ የኪነ ጥበብ ስነ-ስርአት  ላይ  ለመታደም  ችምችም ብለው ይስተዋላሉ።

ከምልምል ወታደሮቹ ገጽታ የሚነበበው ሀገር የማዳን ተስፋና  ቆራጥነት  ወደሰው ይጋባል፤   ተቀላቀሏቸው የሚል መንፈስ ያሳድራል፡፡

ምልምል ወታደሮቹ በውስጣቸው የሚነበበው የእናት  ሀገር ፍቅር፣  እናትን  ከህወሃት ነቀርሳና ሽብር ለመገላገል ያላቸው ወኔ ልብ ይሞላል።

የምልምል ወታደሮቹ ገጽታ የማስደመሙን ሚስጥር ከፍ ያደረገው ደግሞ ለሀገራቸው  መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁ  ሶስት  ወንድማማቾች ከመካከላቸው መገኘታቸው ነው፡፡

አሉላ ዘማች፣ ምንአሉ ዘማችና መርከቡ ዘማች  ይባላሉ።

ምልምል ወታደር መርከብ ዘማች  ሰራዊቱን ለመቀላቀል ያነሳሳው የህወሃት የሀገር ክህደት በፈጠረበት ቁጭት መሆኑን የገለጸው እንዲህ ሲል ነበር ።

"ህውሃት በ27 ዓመት የስልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያን  መጫወቻ አድርጎ ዛሬ  ደግሞ  ጭራሽ  ሊያፈርሳት የከፈተው የሽብር  ተግባር በፍጹም አይሳካም፤ እኛ ወጣት ልጆቿ አለንላት፤ እናሻግራታለን  " ሲል ወደ ሁርሶ ማሰልጠኛ የመጣበትን ምክንያት ገልጻል።

ከአንድ ቤተሰብ ሶስት ወንድማማቾች ሀገር ለማዳንና መስዋዕት ለመክፈል ሲዘምቱ በህይወት ያሉ እናትና አባት በተለይ ደግሞ እናት ስተሸኛቸው አዝናና ተክዛ  አልነበረም ።

ምልምል ወታደር መርከብ  እንዳለው "እናታችን ስትሸኘን 'ወንድ ልጅ ቤትም ሆኖ ይሞታል ፤ ይልቁንም ሂዱና የክብር ሞት በመሞት እናት ሀገራችሁን አድኑ'  በሚል ነበር"  ብላል" ።

ሌላው  በደቡብ ክልል ተወልዶ ያደገውና በአዲስ አበባ በመንግስትና በዓለም አቀፍ  የኮሙዩኒቲ ትምህርት  ቤቶች  በመምህርነትና  በርዕሰ መምህርነት  ሲያገለግል  የነበረው  እንዲሁም  ዛሬ በሁርሶ ማሰልጠኛ ምልምል ወታደር የሆነው  ፍቃዱ አለማየሁ ነው፡፡

ፍቃዱ "እኔ እዚህ የመጣሁት ለሀገሬ ክብር ያለው  ሞት ልሞትላት ተዘጋጅቼ ነው፤  እርግጥ ነው መምህርት ክቡር ሙያ ቢሆንም ይህ እውን የሚሆነው ሀገሬ ከህውሃት አሸባሪ ነጻ ስትወጣ ብቻ ነው" ሲል የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሲል ከሰራዊቱ ለመቀላቀል የወሰነበትን ምክንያት ገልጿል።

የነዚህ ወጣቶች ቆራጥና ሀገር የማዳን ውሳኔ ከተጋባባቸው አንዱ ደግሞ የደቡብ የኪነ-ጥበብ ቡድን አባል ኑረዲን የሴ ተጠቃሽ  ነው፡፡

በጥበብ ሀገራዊ ድል እንዲመጣ መቀስቀስ አንድ ጉዳይ ነው፤ ዛሬ ግን በዚህ  ትምህርት  ቤት   ከሚገኙ ወጣት ምልምል ወታደሮች ታላቅ የሀገር ፍቅር ተጋብቶብኛል፤  እኔም  ለሀገሬ መዳን ህይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ"  ሲል ለራሱ በመወሰን ቃል ገብቷል፡፡

የወጣት ምልምል ወታደሮች ሀገር የማዳን ውሳኔ  ያለልዩነት የሁሉም  ኢትዮጵያዊያን  የዛሬ ውሳኔ ሊሆን ይገባል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም