የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዋ አሜሪካ በአፍጋኒስታን ላይ በሰነዘረችው የድሮን ጥቃት ንጹሃን ተገደሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዋ አሜሪካ በአፍጋኒስታን ላይ በሰነዘረችው የድሮን ጥቃት ንጹሃን ተገደሉ
ነሀሴ 24 ቀን 2013 በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ለሀገራት አስተምራለሁ የምትለው አሜሪካ በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ላይ በሰነዘረችው ጥቃት ንጹሃን መገደላቸው ተገለጸ፡፡
አሜሪካ በካቡል አየር ማረፊያ አቅራቢያ በሰነዘረችው የድሮን ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን አፍጋኒስታውያን መገደላቸውን ዛሬ የወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡
አሜሪካ ትላንት እሁድ በካቡል አየር ማረፊያ አካባቢ በሰነዘረችው የድሮን ጥቃት በትንሹ ሶስት ህጻናትን ጨምሮ ስድስት ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የአይን እማኞችን ጠቅሶ አልጀዚራ ያስነበበ ሲሆን ሲ ኤን ኤንን ጨምሮ አንዳንድ ብዙሃን መገናኛዎች ደግሞ ከአንድ ቤተሰብ አባላት ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ ከነዚህ ውስጥ ስድስቱ ህጻናት መሆናቸውን አስነብበዋል፡፡
ጥቃቱን በተመለከተ የአሜሪካ ማዕከላዊ የጦር ማዘዣ ባወጣው መግለጫ ንጹሃን እንደተጎዱ መረጃ እንዳለው ጠቅሶ፤ “ሰዎችን ከካቡል ለማስወጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል በማሰብ በአካባቢው በርካታ የአጥፍቶ መጥፋት ዕቅዶች ስለነበሩ ነው ጥቃቱን የሰነዘርነው” ሲል ገልጿል። የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
አሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣት የሚፈልጉ አፍጋኒስታውያንን ለማስወጣት ጥረት እያደረኩ በነበረበት ወቅት ባለፈው ሀሙስ የአጥፍቶ ጠፊዎች በአየር ማረፊያው አካባቢ በሰነዘሩት የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 13 ወታደሮቼን ጨምሮ 175 ሰዎች መገደላቸውን ምክንያት በማድረግ ነው በድሮን የታገዘ ጥቃት የሰነዘርኩት ማለቷም ተገልጿል፡፡ከሀሙስ ዕለቱ የአጥፍቶ መጥፋት ጠቃት ወዲህ አሜሪካ በካቡል በድሮን የታገዘ ጥቃት ስትፈጽም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደነገሩት ከሆነ ደግሞ እሁድ የተወሰደው የድሮን ጥቃት በካቡል አየር ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኙ መኖሪያ አካባቢ የአጥፍቶ ጠፊዎች በተሸከርካሪ ላይ ፈንጂ ሲጭኑ በመታየታቸው ተሸከርካሪው በሚሳኤል እንዲመታ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከተሰነዘረው የድሮን ጥቃት በኋላ የበርካታ ህጻናትን አስክሬን መሰብሰባቸውን አህመዱዲን የተባሉ የአይን እማኝ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ እኤአ በ2001 በአሜሪካ የደረሰውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ ወደ አፍጋኒስታን ያስገባቻቸውን ወታደሮች አጠቃላ የምታስወጣበት የመጨረሻ ቀን ነገ ሲሆን ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረበት እኤአ ከነሀሴ 15 ጀምሮ ከ114 ሺህ በላይ አፍጋኒስታውያንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቱ ተገልጿል፡፡