መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ስራ ለተደራጁ ወጣቶች የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ አደረገ

59

ጎባ፣ ነሃሴ 21/2013 (ኢዜአ) መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ በኩታ ገጠም የግብርና አሰራር ለተደራጁ ወጣቶች የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ አደረገ።

ለወጣቶቹ በድጋፍ የተሰጠው የስንዴ ምርጥ ዘር በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ የማህበረሰብ አገልግሎትን ለተጠቃሚ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን ያደረገው መንግስት አርሶ አደሩ ወደ ተሻሻለ የግብርና አሰራር እንዲሸጋገር እያደረገ የሚገኘውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑን አስረድተዋል።

በማህበር ተደራጅተው በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ 28 ወጣቶች 130 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ  ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ምርጥ ዘርና ማዳበሪያው  130 ሄክታር ማሳ የማልማት አቅም እንዳለው አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት በዞኑ ሲናና፣ አጋርፋና ጎሮ ወረዳዎች በ30 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ለተደራጁ ወጣቶች የዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው ተሞክሮውን የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው በክልሉ በመኽር ወቅት 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርት ወቅቱ በሰብል ከሚለማው መሬት ውስጥ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮኑ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የሚለማ መሆኑን አመልክተል፡፡

አቶ ጌቱ እንዳሉት መንግስት የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በክልሉ በዘንድሮ ብቻ ከ1 ሺህ 200 በላይ ትራክተሮችን በረዥም ጊዜ ብድር ለአርሶ አደሩ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፋ ገበያን ማዕከል አድርጎ ለማምረት የአርሶ አደርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁርኝትን በማሳለጥ የቴክኖሎጂን ሽግግር ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የጎሮ ወረዳ ወጣቶች መካከል ሀብታሙ ከበደ ዩኒቨርሲቲው ያደረገላቸው የምርጥ ዘር ድጋፍ በእርሻ ስራቸው እንዲተጉ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ገልጿል።

በባሌ ዞን በ2013/2014 ምርት ዘመን መኽር ወቅት ከ256 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለመሸፈን ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም