በኢሉባቦር ለዘማች ሚሊሺያ ቤተሰቦች ድጋፍ እየተደረገ ነው

83

መቱ ነሐሴ 24/2013 (ኢዜአ) በኢሉባቦር ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ለዘመቱ የሚሊሺያ ቤተሰቦች ድጋፍ እየተደረገ ነው።
በዞኑ ሁሩሙ ወረዳ ለሚገኙ የሚሊሺያ  ቤተሰቦች የምግብ እህልና ዘይት ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን በመቱ ከተማ ደግሞ ለዘማች ቤተሰቦች መኖሪያ  ቤት ተሠርቶላቸዋል።

ድጋፉ የተደረገላቸው የሚሊሻ ቤተሰቦችም ሕብረተሰቡና የመንግስት አካላት እያሳዩዋቸው ላለው አጋርነት አመስግነዋል።

ወይዘሮ ተሚማ እሼቱ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ጠቅሰው የአከባቢው ማህበረሰብም ሆነ የአስተዳደር አካላት እያደረጉላቸው ሰላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

ሕብረተሰቡና መንግስት አብሯቸው ስላለ ስጋት እንደማይገባቸው ነው ወይዘሮ ተሚማ የተናገሩት።
በሁሩሙ ወረዳ የዮቢ ዶላ ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ ኑሪያ አያና በበኩላቸው ባለቤታቸው ሀገር ለማዳን እንደዘመቱ ሁሉ ሕብረተሰቡም በሚያስፈልጋቸው  ሁሉ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

"የሕብረተሰቡ አብሮነት ምን እንሆናለን ብለን ብዙ እንዳንጨነቅ ረድቶናል፤ ለዘመቱትም ፈጣሪ ድሉን ይስጣቸው" ብለዋል።

ወይዘሮ ብርሃኔ ደገፋ ደግሞ "ህዝባችን በሚያስፈልገን ሁሉ ከኛ ጋር ስላለ ብቸኝነት አይሰማንም" ብለዋል።

የአከባቢያቸው ማህበረሰብ እንደሚጠይቃቸውና ችግሮቻቸውንም እየተጋሯቸው እንደሆነም ነው ወይዘሮ ብርሃኔ የተናገሩት።

የያዮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ረጋሳ "የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የዘመቱ ሚሊሺያ ቤተሰቦችን በሚያስፈልጋቸው በመደገፍ ከጎናቸው መሆናችንን መግለፅ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

በመቱ ከተማ ለሚሊሺያ ቤተሰብ አባላት የመኖሪያ ቤት የተሰራላቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ነጋሽ ናቸው።

"ለሀገር ሉዓላዊነት ዘብ መቆማችንን ከምናሳይባቸው ተግባሮች አንዱ ለሚሊሺያ ቤተሰቦችና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በምናደርገው ድጋፍ ነው" ብለዋል።
ለመከላከያ ሰራዊትና ለሚሊሺያ ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም