ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አንድነትን ያጠናክራል - በጎ ፈቃደኞች

64
አሶሳ ነሀሴ 6/2010  ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የክልሉን ህዝቦች ባህል ለማወቅና አንድነታቸውን ለማጠናከር እንደሚረዳቸው አሶሳ የተመደቡ የአገልግሎቱ ተሳታፊ ወጣቶች ገለፁ፡፡ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊ የሆኑ 80 የተለያዩ ክልል ወጣቶች ትናንት አሶሳ ገብተዋል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ለሊሳ ታረቀኝ “በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የምንኖር ወጣቶች  በአሶሳ ከተማ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት መሰባሰባችን በህዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከር ያግዛል'' ብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ አሶሳ መጥቶ እንደማያውቅ የገለፀው ወጣቱ አጋጣሚው የክልሉን ህዝቦች ባህልና አኗኗር ለማወቅ እንደሚረዳው ተናግሯል፡፡ ከደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን እንደመጣ የገለፀው ወጣት ታጋይ ካኒቶ በበኩሉ የወሰን ተሻጋሪ የበጎፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶችን በማቀራረቡ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጿል፡፡ አሶሳ ከተማ የሚኖረው ቆይታም ስለ አካባቢው ቋንቋና ባህል ለማወቅ እንደሚረዳው ተናግሯል፡፡ በአሶሳ ከተማ በሚኖራት ቆይታ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማገልገል መዘጋጀቷን የገለፀችው ደግሞ  የጋምቤላ ክልል ነዋሪ ወጣት አባንግ አግዋ  ናት፡፡ ወጣት ረታ ብርሃኑ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሳተፋ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ወጣቶችን አስተባባሪ ነው፡፡ ወጣት ረታ እንደገለፀው ወጣቶቹ በክልሉ በሚኖራቸው የአስር ቀናት ቆይታ በአካባቢ ጥበቃና ፅዳት፣ በደም ልገሳና በሌሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ፡፡ ከበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ጎን ለጎንም የልምድ ልውውጥና የባህል ትውውቅ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም