በፍትሕ ዘርፉ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማረም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል

1328

ነሐሴ 21 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በፍትሕ ዘርፉ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማረም የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት እንደሚያስፈልግ የፌዴራል የሕግ፣ ፍትሕ፣ የሕግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት አመለከተ።

ኢንስቲትዩቱ ‘ሰው ተኮር ፍትሕ በኢትዮጵያ’ በሚል መሪ ሃሳብ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ለሶስት ቀናት የሚቆይ ምክክር እያካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሒል ከተሰኘ የኔዘርላንድስ ድርጅት ጋር በመተባበር የክልሎችን የፍትሕ ስርዓት በተመለከተ ያካሄደው ጥናት ይፋ ሆኗል።

ጥናቱ በፍትሕ ዘርፉ የሚስተዋሉ ቁልፍ ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል።

በዚህም የመሬት ጉዳይ 38 በመቶ፣ ወንጀል ነክ ጉዳዮች 26 በመቶ፣ ከጎረቤት ጋር የተያያዙ ችግሮች 15 በመቶ፣ የቤተሰብ ጉዳይ 12  በመቶና የቤት ውስጥ ጥቃት 9 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው አመላክቷል።

በአጠቃላይ የፍትሕ ስርዓት 40 በመቶ የኢትዮጵያ አዋቂ የኅብረተሰብ ክፍል በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ወይም ከዛ በላይ የሕግ ችግሮች እንደሚያጋጥሙት ጥናቱ አሳይቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ የፍትሕ ጉድለት ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚፈልግና መንግሥታትን ከሚፈታተኑ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያም የፍትህ ሥርዓት ጉድለት እንደሚስተዋልና በጥናቱም መመላከቱን ገልጸው፤ በተለይም የመሬት ጉዳይ አቢይ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ አክለዋል።

የዘርፉን ችግሮች መፍታት የፍትሕ ተቋማት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚሻም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም ከዘመናዊ ተቋማት ባሻገር ባሕላዊ የፍትሕና የሕግ ሥርዓቶችን ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።