የአገር አቀፍ የከተማ ቤቶች መረጃ አስተዳደር ሶፍትዌር ይፋ ሆነ

62

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 21/2013(ኢዜአ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የአገር አቀፍ የከተማ ቤቶች መረጃ አስተዳደር የመረጃ ቋት/ሶፍትዌር/ን ይፋ አደረገ።

የመረጃ ቋቱን ይፋ ያደረጉት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ መተግበሩ በአገሪቷ የሚገኙ ቤቶችን መረጃዎች ለማወቅና ለአስፈላጊው ስራ ለማዋል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ይፋ የተደረገው የመረጃ ቋት ቀድሞ የነበረውን የመረጃ አያያዝ ችግር ከመፍታት ባሻገር ብልሹ አሰራርን መከላከልና ማስቀረት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት።

የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው ዜጎች በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያግዛል።

በአጠቃላይ ሶፍትዌሩ የቤቶች አስተዳደርን ያቀላጥፋል፣ በአገሪቷ የሚገኙ ቤቶችን ትክክለኛ መረጃ ማወቅ እንዲሁም ቤትና ቤት ነክ መረጃዎችን በአግባቡ ማደራጀትና መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።

የመረጃ ቋቱ በሚኒስቴሩ የሚገኝ ሲሆን ክልሎች በራሳቸው የይለፍ ቃል በመግባት መጠቀም ይችላሉ።

በታህሳስ አይሲቲና ኮንሰልተንሲ ሰርቪስ የለማው ይህ የመረጃ ቋት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የደህንነት ድጋፍ ተደርጎለታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም