ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት በአጭር ጊዜ ይጠፋል

348

ነሐሴ 20/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት በዜጎች ትብብር በአጭር ጊዜ ይጠፋል ሲሉ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ተናገሩ።

ዶክተር አለሙን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍሰሀ ወልደሰንበት፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንዳለ ሀብታሙና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በግንባር ተገኝተው ሰራዊቱን አበረታተዋል። 

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደርም ለሰራዊቱ ያዘጋጃቸውን ሰንጋዎችና በጎች አስረክቧል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ‘እኔ የማላስተዳድራትና የማላዛት ሀገር ትፍረስ’ በሚል እብሪት ጦርነት ከፍቷል።

“አሸባሪው ቡድን በሀሰት፣ በበደልና ግፍ የከፈተብንን ጥቃት የመከላከያ ሰራዊቱ እውነትና ፍትህን ታጥቆ በድል እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም” ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት በዜጎች ትብብር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠፋም ተናግረዋል።

ህፃናትን አስገድዶ ወደ ጦርነት በማስገባት የትግራይ እናቶችን የሚያስለቅሰውን ቡድን ማጥፋት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ የእብሪት ሃይሎች ተጠራርገው ይወገዳሉ ነው ያሉት ዶክተር አለሙ።

የመከላከያ ሰራዊቱም ከደጀን ህዝብ ጋር በመሆን የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ የአባቶቹን ገድል እንደሚደግም ገልፀው፤ የኢትዮጵያ ህልውናም እውን ይሆናል ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ፍሰሃ ወልደሰንበት ሰራዊቱ በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ በጠላት ላይ ከባድ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

“እናንተ ኢትዮጵያን ለዘመናት ስትጠብቁ የኖራችሁ ጀግኖች ናችሁ፤ ወደ ፊትም ሀገራችሁን በጀግንነት ስታስከብሩ ህዝቡ ከጎናችሁ እንደማይለያችሁ እናረጋግጣለን” ብለዋል።

በየዘመናቱ ኢትዮጵያ ፈተናዎች ሲገጥሟት ከፈተና ያወጧት ጀግኖች ልጆቿ እንደነበሩ ገልጸው፤ “ዛሬም ከገጠማት ፈተና ለመውጣት ሰራዊቷ ድል ያስመዘግባል” ነው ያሉት።

አርቲስት ተሾመ አየለ /ባላገሩ/ በበኩሉ “የመከላከያ ሰራዊት አባላት የጀግኖች ልጆች በመሆናችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሌም እንኮራባችኋለን” ብሏል።

ኢትዮጵያዊያነት አንድነት፣ ህብረትና መተባበር መሆኑን ገልፆ፤ ኢትዮጵያን ካላጠፋሁ ከሚል አሸባሪ ሃይል የመጠበቅ ኅላፊነት እንደተጣለባቸውም ገልጸዋል።