የሰላም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

376

ነሐሴ 20/2013 (ኢዜአ) የሰላም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት ደማቸውን በመለገስ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይም ድጋፍ አደረጉ።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ለሠራዊቱ ግዳጅ አፈጻጸም ስኬታማነት በማንኛውም መልኩ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።    

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሸኔ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ላይ አደጋ ለመደቀን እያደረገ ያለውን ጥረት ኢትዮጵያውያን ለመመከት እየሄዱበት ያለው መንገድ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ያለ አካል ራሱ ይፈርሳል የሚለውን መርህ በመከተልም ሠራዊቱ ውድ ህይወቱን እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ድጋፉን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።  

አገራችን በእርዳታና በድጋፍ ሰበብ ሉዓላዊነቷን መዳፈር “ቀይ መስመር” መሆኑን አስቀምጣለች፤ ለዚህ ደግሞ መተማመኛው ህዝቡ ነው ሲሉም አክለዋል።      

የሰላም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማትና ሠራተኞች ከደመወዛቸው 40 ሚሊዮን 55 ሺህ ብር በገንዘብ እንዲሁም 3 ሺህ 500 ፍራሽ፣ 2 ሺህ 900 ብርድ ልብስ፣ 6 ሺህ 900 አንሶላ እና 1 ሺህ 900 አልጋ ድጋፎችን ማስረከቡን አስረድተዋል።    

ምግብ ነክ ከሆኑ ድጋፎች ጋር በተያያዘም ሚኒስቴሩ ቆሎና ቴምርን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉ ድጋፎችን ማድረጉን ጠቁመዋል።

በግንባር ከመከላከያ ጋር የተሰለፉ ሦስት የተቋሙ ሠራተኞች መኖራቸውን የገለጹት ወይዘሮ ወርቅነሽ ተጨማሪ ሰባት ሠራተኞች ደግሞ ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅተዋል ብለዋል።   

ለመከላከያውና ጸጥታው ኃይሉ የሚደረገው ድጋፍ በዚህ የሚያበቃ ባለመሆኑ በየጊዜው ይቀጥላሉ ብለዋል።  

የመከለከያ ሠራዊት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴል ጄነራል አስረስ አያሌው፤ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መንቀሳቀሳቸው ውጤታማ ሥራ እንዲከናወን ማድረጉን ተናግረዋል።  

የሰላም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ለሠራዊቱ የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸው ለሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በደም ልገሳው ላይ የተሳተፉ የሚኒስቴሩ ሠራተኞች፤ ሠራዊቱ ከምንም ጊዜውም በላይ ድጋፍ የሚፈልግበት ጊዜ ነው፤ ድጋፋችንንም እንቀጥላለን ብለዋል።    

አቶ ፍሬሰንበት ወልደ ትንሳኤ፤ አገራችንን ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመከላከል ደሙን እያፈሰሰ ላለው ሠራዊት ደም መለገስ ሁላችንም ልናደርገው የሚገባው ነው ብለዋል።

“ስለማይቻል እንጂ በየቀኑ ለሠራዊቱ ደሜን ብሰጥ ደስተኛ ነበርኩ” ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሽመልስ በዳሶ ናቸው።