የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻችን ይመለሱልን...የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

65
ሰቆጣ ነሀሴ 5/2010 በዞኑ የሚታዩት የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጣን ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአማራ ክልል የዋግ ህምራ ዞን የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ በወቅታዊ ጉዳዮች እና በዞኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ የስራ ሃላፊዎች ጋራ ውይይት አድርገዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ መንግስት ባየ እንዳሉት “የተከዜ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ጋር የሚያስተሳስር የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ የዞኑ ማህበረሰብ በአሳ ምርት ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም’’ብለዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኘው የተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል የሚሰጠው አገልግሎት ከዞኑ ማህበረሰብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አይደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። “የሆስፒታሉ ደረጃ እንዲሻሻልልን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘታችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተላክን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት እያባከንን እንገኛለን ’’ ብለዋል፡፡ አቶ ሰለሞን መሃመድ በበኩላቸው የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ሊቀረፍ የሚችል ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች በበጀት እጥረት ምክንያት ተፈጻሚ ባለመሆናቸው የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሳይረጋገጥ ቀርቷል ያሉት አቶ ሰለሞን “የክልሉ መንግስት የአካባቢውን የልማት ችግር ሊቀርፍ የሚችል ስርዓት ሊዘረጋልን ይገባል” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “የብሄረሰቡን ቋንቋና ባህል ለማሳደግ ተቋቁሞ የነበረው የኽምጣጛ ማእከል ወደ ቀድሞው ስራ ሊመለስ ይገባል” ያሉት ደግሞ ቀሲስ ሃይሌ ብርቱ ናቸው። “እየተገነባ ያለው የሰቆጣ ብልባላ የአስፓልት ስራ ፕሮጀክት የጥራት እና የደረጃ መሻሻል ጥያቄ በተደጋጋሚ ብናቀርብም ምላሽ የሚሰጠን አልተገኘም” ብለዋል፡፡ ወጣት ሃብታሙ መንግስቴ በበኩሉ በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ ያለውን የስልክ ኔት ወርክ አገልግሎት ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊቀመጥለት ይገባል ብሏል፡፡ የሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃና ሰነድ ክትትል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያለው ወጣቱ በወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ላይ ያሉ ችግሮችም እንዲፈቱ ጠይቋል። የክልሉን መንግስት ወክለው በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጅ እንዳሉት በከተማዋ እየተስተዋለ ያለውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል። እየተስተዋለ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል የሚያስችል በውሃ ቢሮ በኩል የዲዛይን ጥናት የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ “የክልሉ መንግስት በወሰነው መሰረት የተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ሆሲፒታልን ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል የማስፋፊያ ግንባታ ከማከናወኑም በላይ በሰው ሃይል እንዲሟላ በእቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡ በዞኑ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ  አምስት የተለያዩ የመንገድ ስራዎች በክልሉ እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው ከተከዜ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ጋር የሚያስተሳስሩ መንገዶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። “የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈጥሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በግምገማ በመለየትና የማስተካከያ እርምጃ  በመውሰድ ለውጡን በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን”ብለዋል። የአማራ ሰማእታት ሀውልት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አወጣ ገብሩ በበኩላቸው ራሱን ችሎ ተቋቁሞ የነበረው የቋንቋ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በትምህርት መምሪያ በኩል በአንድ ሂደት እንዲዋቀር ተደርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ዳር ለማድረስ በሚደረገው ጥረት በተለይ የዞኑ ማህበረሰብና ወጣቱ ለሃገር ልማትና ሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በሰቆጣ ከተማ ትላንት በተካሔደው የውይይት መድረክ ላይ ከከተማዋና አካባቢው የተወጣጡ ወጣቶች፣የአመራር አካላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም