የጥቁር ገበያን ለመከላከል የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል - ምሁራን

61
አዲስ አበባ  ነሀሴ 5/2010 በኢትዮጵያ የጥቁር ገበያ የገንዘብ ልውውጥን ለመከላከል የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ በስፋት መሠማራት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራኖች ገለጹ። በተለይም በንግዱ ዘርፍ ውድድርን መሰረት ያደረገ የገበያ ሥርዓት በመፍጠር በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፍላጎትና አቅርቦትን ማመጣጠን እንደሚገባም አሳስበዋል። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ካሳ ተሻገር እንደተናገሩት፤ የጥቁር ገበያ የገንዘብ ልውውጥ ዋነኛ መንስዔ የገበያ ሥርዓቱ መፋለስ የሚታይበት መሆኑ ነው። የገበያ ሥርዓቱ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ውድድርን መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ ያለአግባብ ገበያውን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ እድል የሰጣቸው እንደሆነም አመላክተዋል። ይህም ደግሞ የገበያ ሥርዓቱ እንዲጓደል በማድረግ ለጥቁር ገበያ የገንዘብ ልውውጥ በር ከፍቶ ውስን ሰዎች ብቻ ከውጭ እቃዎችን  እንዲያመጡ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል። የውጭ ምንዛሬም ሕገ-ወጥ በሆነ መልኩ ወደ አገር እንዲገባ ያደርጋል፤ ውድድርን ያስቀራል፣ ይሄም የኑሮ ውድነት በመቀስቀስ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ይጎዳል ነው ያሉት። በመሆኑም መንግሥት ችግሩን ለማቃለል የውጭ ምንዛሪ በሚያስቀረው የወጭ ንግድን መሰረት ያደረገ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ። ካዛ ባለፈ በአገር ውስጥ የተዘረጋውን የታክስ ሥርዓትና እንዲሁም የገበያ ሥርዓቱን ማዘመን እንደሚገባ ጠቁመዋል። ሌላኛው የዘርፉ ባለሙያና የኢኒሼቲቭ አፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና፤ በአንጻሩ የጥቁር ገበያ የገንዘብ ልውውጥ አንድም ችግር ነው በሌላ በኩል ደግሞ ሊኖር የሚገባ ነው ይላሉ። ይሁንና በጥቁር ገበያ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሬ የልውውጥ መጠኑ ከመደበኛ ባንኮች ጋር ከፍተኛ ልዩነት ካለው ምጣኔ ኃብቱን በማሳደግ ልዩነቱን ማጥበብ ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም ደግሞ ዋነኛ ችግር አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኝላት የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፍ ላይ የምታደርጋቸው ተሳትፎ ያን ያክል ውጤታማ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም መንግሥት ለእነዚህ ዘርፎች ቅድሚያ በመስጠት ምጣኔ ኃብቱን በማሳደግ ችግሩን መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል። በ2010 በጀት ዓመት ከአገራዊ የውጪ ንግድ አፈጻጸም 2 ነጥብ 83 ቢሊዮን ዶላር ገቢ  ተገኝቷል፤ ይህም ከዕቅዱ 54 በመቶ መሆኑ የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል። ይኸው የበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ አፈጻጻም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 2 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 43 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም