በአማራ ክልል አዳዲስ ወጣት ባለሃብቶችን ለመፍጠር የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

90
ደብረ ብርሃን ነሃሴ 4/2010 በአማራ ክልል በጥቃቅንና አነስተኛ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከር አዳዲስ ወጣት ባለሃብቶችን ለመፍጠር የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ ባለፉት ዓመታት በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ዘርፍ ተሰማርተው ለውጥ ያመጡ ኢተርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሃብትነት የማሸጋገሪያ መድረክ ተካሂዷል። የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ድረሴ እሸቴ በመድረኩ እንደገለጹት አዳዲስ ወጣት ባለሃብቶችን ለማፍራት የተጠናከረ የመንግስትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ይጠይቃል። በዓለም ገበያና በሀገር ውስጥ ምርት ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው በእድገት ተኮር የልማት ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በጥራትና በብዛት አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ በማስቻል ነው። ሀገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር የምታደርገውን ጥረትም ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ልከው ምንዛሬ በማምጣት፣ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጅዎችን አምርተው በመተካትና የክህሎት ሽግግር በማምጣት የሚኖረቸው ሚና የጎላ ነው። በደብረ ብርሃን ከተማ አሁን ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩት ኢተርፕራየዞችም በቀጣይ በአምራች ኢንዱስትሪው እንዲሰማሩ የሚደገፉ መሆናቸውን አስረድተዋል። የደብረ ብርሃን ጥቃቅንና አነስተኛ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረህይወት እንዳሉት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተጠናከረ ስራ በመከናወኑ መስፈርቱን ያሟሉ ሰባት ኢንትርፕራይዞች ወደ ታዳጊና መካከለኛ ባለሃብትነት ዛሬ ተሸጋግረዋል። ኢንተርፕራይዞቹን ማሸጋገር የተቻለውም ከ1 ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ውጤታማ መሆናቸውን በራሳቸውና በተዋቀረው ቡድን በመረጋገጡ ነው፡፡ " ወደ ባለሃብትነት የተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች በማንፋክሪንግ ዘርፍ ብረታብረት፣ ጨርቃጨርቅ፣ እንጨት ስራና ምግብና ምግብነክ ሙያ ላይ የተሰማሩ ናቸው" ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው 8 ሺህ 842 ወጣቶች መካከል 551 የሚሆኑት በኢንተርፕራዝ የተደራጁ ናቸው፡፡ ከተሸጋገሩት የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች መካከል ወጣት ፍቃደ ንጉሴ ከ38 ጓደኞቹ ጋር በ125 ሺህ ብር ካፒታል በባልትና ማኅበር ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ እድል ከመፍጠራቸው በላይ ካፒታላቸውን ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ በማሳደግ ወደ ባለሃብትነት ለመሸጋገር መብቃታቸውን ገልጿል፡፡ ዕድገታቸውንም በዚህ ሳይገቱ በቅርቡ በዘመናዊ መንገድ ክክ የሚያበጥር ማሽን ለመግዛት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ወጣት መላኩ በትረ በበከሉ በ2005 ዓ.ም. በ150 ሺህ ብር ካፒታል ልብስ ስፌት ኢንተርፐራይዝ ሥራ በመጀመር የሴትና የወንድ ዘመናዊ አልባሳትን በማዘጋጀት ለገበያ በማቅራብ ትርፋማ መሆን እንደቻለ ገልጿል፡፡ አሁን ላይ ካፒታሉንም አንድ ሚሊዮን 700ሺህ ብር በማድረስ ለ30 ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቁሞ በቀጣይ ስራውን አስፋፍቶ ለተሻለ ውጤማነት በትጋት እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ መልኩ አምስት ኢንተርፕራይዞችን ወደ ባለሃብት መሸጋገራቸው ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም