ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ የሆነው የሳማንታ ፓወር መግለጫ

193

ነሀሴ 14/2013 (ኢዜአ) የአሜሪካ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት ዩ ኤስ ኤይድ ዋና ሀላፊ ሳማንታ ፖወር ከ15 ቀናት በፊት በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የእርዳታ ስርጭት ያለበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።

ሀላፊዋ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ትንኮሳ በአፋር ክልል ከ76 ሺህ በላይ እንዲሁም በአማራ ክልል ከ150 ሺህ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን መረጃ እንዳላቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ወደ አጎራባች ክልሎች ወረራና ጥቃት መፈጸሙ አሜሪካ በከፍተኛ ስጋት እየተከታተለችው ስለመሆኑም ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ነው።

በትግራይ ክልል ላጋጠመው የሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ አቅርቦት እንዲሆን አሜሪካ ተጨማሪ 45 ሚሊዮን ዶላር ስለመስጠቷ የተናገሩት ሀላፊዋ የእርዳታ መጋዘኖችን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው የምግብ ክምችት ከትግራይ በተጨማሪ ለሌሎች አካባቢዎች ጭምር በቂ መሆኑን ምስክርነት ሰጥተውም ነበር።

እውነታው ይህ ቢሆንም ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ በትግራይ ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን በመጥቀስ በክልሉ ያሉ የዩ ኤስ ኤይድ እና ሌሎች ድርጅቶች የእርዳታ ምግብ ማከማቻ መጋዘኖች ባዶ ናቸው በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

አያይዘውም “እጥረቱ የተከሰተው ምግብ ባለመኖሩ ምክንያት ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በማደናቀፉ ነው" ሲሉ ይከሳሉ ።

መንግስት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ የነበረው በትግራይ ያለው አርሶ አደር ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን እንዲሁም የእርዳታ ስራው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሰራጭ በማሰብ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳውቋል።

ይሁን እንጂ አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ሀገር የማተራመስ ፍላጎቱን ለማሳካት በአፋር እና በአማራ ክልሎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።

በዚህ ጥቃት ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ከቤት ንብረታቸውም ተፈናቅለዋል። ይህንን አስመልክቶ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ሀላፊ ሳማንታ ፖወር በአሁኑ መግለጫቸው ስለተፈናቀሉትም ይሁን ህይወታቸውን ስላጡ ዜጎች አንዲትም ነጥብ አላነሱም።

ሳማንታ ፖወር አሁን ያወጡት መግለጫ የሚመሩት ድርጅትም ይሁን መንግስታቸው አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እውቅና ለመስጠት ካለመፈለጋቸውም በላይ በአሸባሪው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አይተው እንዳላዩ በማለፍ ኢትዮጵያውያንን በሚያስቆጣና ጥርጣሬ በሚያጭር መልኩ ለሽብርተኛው ቡድን ያላቸውን አጋርነት የሚያመላክት ገሀድ እውነት አሳይተዋል። ይህም ሆኖ ኢፍትሃዊውን ውግንና መላው ዓለምና የኢትዮጵያ ወዳጆች በአፅንኦት እየተከታተሉት ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም