ለሃዋሳ መዋቅራዊ የከተማ ፕላን ክለሳ እየተደረገ ነው

1713

ሀዋሳ ነሃሴ 4/2010 የሃዋሳ ከተማን የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መዋቅራዊ የከተማ ፕላን ክለሳ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።

ከተቆረቆረች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረችው ከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን የሚባል እድገት ከተመዘገበባቸው ከተሞች ውስጥ ትጠቀሳለች፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ከተማ እየሆነች የመጣችው ሀዋሳ ከዕድገቷ ጋር ተያይዞ የነዋሪዎቿ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው።

በእዚህም ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ማህበራዊ ጥያቄዎች በነዋሪዎቿ እየተነሱ መጥተዋል፡፡

የሃዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ ሃዋሳ በፕላን ከሚመሩ የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ መሆኗን ገልጸው ከተማዋ በአስር ዓመት የሚከለስ የከተማ ፕላን አሰራር እንደምትከተል ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም አምስተኛው መዋቅራዊ የፕላን ከለሳ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ፣ ይህም የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮቿን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከተማዋ ላለፉት10 ዓመታት በተቀናጀ የከተሞች ፕላን ስትመራ መቆየቷን አስታውሰው የፕላን ክለሳ ሥራው በከተማው አስተዳዳርና በተባበሩት መንግስታት “ሀብታት”  ፕሮግራም ድጋፍ የሚከናወን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ይመኙሻል ገለጻ መዋቅራዊ የክለሳ ፕላኑ መንገድ፣ አረንጓዴ ልማት፣ የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቦታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡

የከተማው አስተዳደር የፕላን ክለሳ ሥራውን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ጥናት በማድረግ በራሱ አቅም ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ከባለሙያዎች አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን በዘርፉ ከ40 ዓመታት በላይ ተግባራዊ የሆነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)  ሃብታት ፕሮግራም ባለሙያዎች የማገዝ ስራ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

“ሌሎችም እንደ ጃይካ እና ሲደ የተሰኙ የጃፓንና ስውዲን አገራት ድርጀቶችም ሥራውን ለማገዝ ፈቃደኝነታቸውን ገልፀዋል” ብለዋል፡፡

ለሥራው የክልልና የፌዴራል የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር በቅርበት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጇ፣ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ሥራውን ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመድ ሃብታት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊሉ ገብረስላሴ በበኩላቸው ቴክንካዊ ድጋፍ ለማድረግ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት አቅም የመገንባትና መረጃ የመተንነተን ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡

የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ የከተማዋን እድገት ያማከለ የፖሊሲ፣ የህግ፣ የኢኮኖሚና የዲዛይንና የፕሮጅክቶች አተገባበር ላይ መሰረት ያደረገ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

የከተማው ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ በበኩላቸው እንዳሉት ሃዋሳ ባለፉት ዓመታት በፕላን መመራቷ ከተማዋ የሚያስፈልጋትን እድገትና መሰረተ ልማት በተሳለጠና በአግባቡ ለማሟላት አቅም ሆኗታል፡፡

አዲስ የሚሰራው መዋቅራዊ ፕላን ከተማዋን በሚፈለገው ልክ የንግድ፣ የቱሪዝምና የኢንዱስትሪ ከተማ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተለያዩ የግል ባለሃብቶች የሚጠይቁት የኢንዱስትሪ ልማት ጥያቄን በተሻለ ለመመለስ እንደሚያግዝና ለአሰራር የሚያመች ፕላን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የክለሳ ፕላኑ ከተማዋን ይበልጥ ለነዋሪው ውብ፣ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አካል እንደሆነም አስረድተዋል፡

ፕላኑ የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት በተዘጋጀ ሰነድ ላይ የከተማው ነዋሪዎች፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ባለሙያዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ከተማዋ ከእዚህ ቀደም አራት ጊዜ ፕላን የተሰራላት ሲሆን የመጀመሪያው በ1949 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት መሰራቱ ታውቋል፡፡