የባለቤቱን ህይወት ያጠፋው ግለሰብ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

2822

አዳማ ነሃሴ 4/2010 የባለቤቱን ህይወት ያጠፋው ግለሰብ  በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ  ቤት  አስታወቀ፡፡

ግለሰቡ በአዳማ ሉጎ ክፍለ ከተማ ጋራ ሉጎ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቀጠና 15 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለቤቱን በአሳቃቂ  ሁኔታ በስለት መግደሉን በማስረጃ ተረጋግጦበታል።

ሙሃዲን ደንበል የተባለው ይሄው ግለሰብ ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለው ሰኔ 23 /2010 ዓ.ም. ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ከሩብ  አካባቢ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ነው፡፡

ድርጊቱን የፈጸመውም የቤቱን  እቃ አውጥቼ በመሸጥ እጠቀምበታለሁ ብሎ ሲነሳ ባለቤቱ ባለመፍቀዷ በተፈጠረ ፀብ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ግለሰቡ በፖሊስ ተይዞ  የምርምራ ሂደቱን በማጠናቀቅ ለአዳማ ልዩ ዞን አቃቤ ህግ በመላክ ክስ ተመስርቶበታል፡፡

የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍድር ቤት ዳኛ አቶ ናኦል አሰፋ እንዳስረዱት ግለሰቡ በባለቤቱ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ የግድያ ወንጀል በሰውና በሰነድ መስረጃ ተረጋግጦበታል፡፡

ክሱን እንዲከላከል እድሉ ቢሰጠውም ባለመቻሉ  ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት  ተገቢና ያስተምራል ያለውን  የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቀዋል፡፡